የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የዳውሮኛ ቋንቋ በመጀመሪያ ድግሪ ማስተማር ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የዳውሮኛ ቋንቋ በመጀመሪያ ድግሪ ማስተማር ጀመረ
ሶዶ ግንቦት 8/2011 ዓ.ምበዳውሮኛ ቋንቋ በመጀመሪያ ድግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ።
በዩኒቨርስቲው የዳውሮ ተርጫ ካምፓስ የዳውሮኛ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አብርሃም ቡልቻ ለኢዜአ እንደገለጹት የዳውሮኛ ቋንቋ ማስተማር የጀመሩት ካለፈው የካቲት ወር አንስቶ በመደበኛ መርሃ ግብር በሙያው ተመርቀው በመምህርነት እያገለገሉ ያሉ 32 መምህራንን በመቀበል ነው።
የትምህርቱ መሰጠት በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት የአካባቢውን ባህል፣ወግና ልማዱን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ያስችላል።
የካምፓሱ ዲን ዶክተር ሽመልስ አርጋው በበኩላቸው ካምፓሱ ከተከፈተ ጀምሮ ህብረተሰቡ በአካባቢው ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ ሲጠይቅ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በየዓመቱ የተማሪዎችን የቅበላ አቅም በመጨመር የትምህርት ክፍሉን በግብዓትና በሰው ኃይል ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በቀጣይ የአከባቢውን ህብረተሰብ፣የዘርፉን ባለሙያዎች፣ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች በማሳተፍ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች የተለያዩ የህትመት ስራዎችን በማዘጋጀት ዘርፉን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የዳውሮኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ባንቲሁን ባረና በዲፕሎማ ተመርቆ የመማር ማስተማር ስራ ሲሰራ እንደነበር አስታውሶ በዩኒቨርሲቲው በተፈጠረው እድል የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቱን እየተከታተለ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
ትምህርቱ በድግሪ ደረጃ መሰጠት መጀመሩ በአካባቢው ማህበረሰብ የሚነገሩ ታሪኮችን በጽሑፍ ለማስቀመጥ፣የተጻፉትን ደግሞ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች በመተርጎም ባህሉን ለማዳበርና አከባቢውን ለማስተዋወቅ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጿል።
ተማሪ ፍሬገነት ተስፋዬ እንዳለው ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ቋንቋ ትምህርት መስጠት ባለመጀመሩ በነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታዎች ሲነሱ ነበር፡፡
የትምህርት ዕድሉን በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን ተናግሮ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በማቅረብ ለቋንቋው እድገት የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።
በመደበኛና በዕረፍት ቀናት በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ የሚገኘው በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የዳውሮ ተርጫ ካምፓስ የተከፈተው በ2008 ዓ.ም እንደሆነ ታውቋል።