ቀጥታ፡

የወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና በኦሮሚያ ክልል ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2011 የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ከግንቦት 14 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ በሚገኘው የወጣት ማዕከል ይካሄዳል።

በሻምፒዮናው ከዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በሁለቱም ጾታዎች በአጠቃላይ 132 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በወንዶች ከ54 እስከ 80 ኪሎ ግራም፣ በሴቶች ከ46 እስከ 67 ኪሎ ግራም ሻምፒዮናው የሚካሄድባቸው የውድድር ዘርፎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሻምፒዮናው ዓላማ በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመመልመል ነው።

ከሻምፒዮናው የተመለመሉ ተወዳዳሪዎች በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካተው ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋልም ብለዋል።

በቀጣይነትም እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2020 በቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛው የኦሎምፒክ ውድድር ለመሳተፍ በሚደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎችም የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለማግኘት እንደሚረዳም ተናግረዋል።

ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የውድድር አማራጮችን ከማስፋት አንጻር፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ያላቸውን አቋም እንዲፈትሹና የባህልና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉም ሻምፒዮናው ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በሻምፒዮናው እንዲሳተፉ ለሁሉም ክልሎችና ለሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በደብዳቤ ያሳወቀ ሲሆን እስካሁን ድረስ ከሶማሌ ከልል ውጭ ሁሉም በሻምፒዮናው ላይ አንደሚሳተፉ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና በሁለት ዓመት አንዴ የሚካሄድ ውድድር እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው በቀጣይ ጊዜያት ሻምፒዮናውን በየዓመቱ ለማካሄድ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ፌዴሬሽኑ ሻምፒዮናውን ከሞሐ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር ጋር በመተባበር እንደሚያዘጋጅም ተገልጿል።

 የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና እስከ ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።

ከሁለት ዓመት በፊት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ በተካሄደው የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና የኦሮሚያ ክልል በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።

የኮሪያ የባህል ስፖርት በሚል የሚታወቀው ወርልድ ቴኳንዶ ከሰውነት ፍልሚያ ባሻገር ጥበባዊ ስልቶችን ያካተተ ክንዋኔ ሲሆን አእምሮና ሰውነት ማሰልጠንን ጨምሮ ህይወትን በአግባቡ ለመምራት የሚያግዝ የስፖርት ዓይነት እንደሆነም የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በ1995 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን ስፖርቱ ከአትሌቲክስ በመቀጠል በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ውጤት በማስገኘት አገሪቷን በማስጠራት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም