በተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ

68

ደብረማርቆስ  ግንቦት 7 /2011ዓም በምስራቅ ጎጃም ዞን በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ በደረሰ የተሽከረካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት መለፉን ፖሊስ አስታወቀ። 

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ  የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው ዛሬ ከቀኑ አምስት ሰዓት ተኩል አካባቢ  ነው።

"ከወረዳው ቀበሌ 022 እንጨት ጭኖ ወደ ግንደወይን ከተማ በመጓዝ ላይ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-08007 ኢ.ት የሆነ ከባድ የጭነት ተሽከረካሪ በመገልበጡ አደጋው ደርሷል" ብለዋል።

በአደጋው ጋቢና ተሳፍረው የነበሩ አራት ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ማለፉን ያመለከቱት ኢንስፔክተሩ አስከሬናቸው ቤተሰቦቻቸው እንዲረከቡ መደረጉን አስታውቀዋል ።

አደጋውን ያደረሰው አሽከርካሪ ለጊዜው በመሰወሩ ፖሊስ ክትትል እያደረገበት መሆኑን ገልፀዋል ።

እንደ ኢስፔክተሩ ገለጻ የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ነው።

በዞኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በደረሱ የተሽከርካሪ አደጋዎች የ116 ሰዎች ህይወት ማለፉ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም