ቀጥታ፡

የኔዘርላንድ ንግስት ማክሲማ ከኢትዮጰያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2011 የኔዘርላንድ ንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፋይናስ ልማት አምባሳደር ንግስት ማክሲማ ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ጋር በኢትዮጵያ ፈጣንና ውጤታማ የፋይናንስ ተደራሽነት ስትራቴጂን መተግበር በሚቻልበት መንገድ ላይ መከሩ።

ንግስቲቷ በማደግ ላይ ባሉ አገራት የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ ማድርግ በሚቻልበት በተለይም በገጠር አርሶ አደርና አርብቶ አደር ማህበረሰብ ዘንድ የማይክሮ ፋይናንስ ተደራሽነት እንዲስፋፋ በሚያከናውኑት ተግባር ይታወቃሉ።

በዚህ ረገድም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፋይናንስ ልማት አምባሳደር በመሆን እያገለገሉ ናቸው።

የንግስቲቷ የኢትዮጵያ ጉብኝት ዓላማም በአገሪቱ የፋይናንስ ተደራሽነትን ፈጣንና ውጤታማ በሆነ መልክ ተግባራዊ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማገዝ በሚቻልበት መንገድ መምከር ነው።

በአሁኑ ወቅት ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ለፋይናንስ አገልግሎት መጠቀምንና በአጠቃላይ ፋይናንስ ተደራሽነትን እውን ለማድረግ የልማት አጋሮች ምን ድጋፍ ማድርግ ይችላሉ በሚሉ ጉዳዮች ላይም ከንግስቲቱ ጋር መወያየታቸውን የባንኩ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ገልፀዋል።

አክለው ንግስቲቷ አብረዋቸው የሚሰሩት የዓለም ባንክ፣ የቢልጌትስ ፋንዴሽን እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በኢትዮጵያ አሁን ባለው የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ህዝቡ በስፋት በመሳተፍ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር በሚቻልበት ላይ የበለጠ እንዲሳተፉ የበኩላቸውን ሚና ለመጫወት ቃል መግባታቸውን አመልክተዋል። 


እነዚህና ሌሎች ተቋማት በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመደጋፍ ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።


"እስከ አሁን ባለን ግምገማ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ተመድ፣ የዓለም ባንክ፣ የቢልጌትስ ፋንዴሽና ሌሎች ተቋማት ለመደገፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍላጎታቸውን እያሳዩን ይገኛሉ፣ ኢትዮጵያም ይህን በበለጠ ለመጠቀም እየሰራች ነው" ብለዋል ዶክተር ይናገር።

ንግስት ማክሲማ በበኩለቸው ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ጋር በፋይናስ ተደራሽነት ዙሪያ እየሰሩ መሆኑን ገለጸው አሁንም ዘርፉን በበለጠ ለማጎልበት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድጋፎች በሚገኙበት መንገድ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ዛሬም የሞባይል ባንኪንግ፣ የብድር አሰጣጥ፣ የፕራይቬታይዜሽን አገልግሎትን፣ የኢንሹራንስና የማይክሮ ፋይናንስ ዘርፎችን አሰራር ቀልጣፋና ፈጣን ለማድረግ የሚያስችሉ የቴክኒክ ድጋፎች በሚመቻቹበት ስልት ላይ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መምከራቸውን ንግስቲቱ ጠቁመዋል።

ንግስቲቷ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ የመጡት ትናንት ነው።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያዊያን የኤሌክትሮኒክ ባንክን፣ ኢንሹራንስን፣ ብድርን ጨምሮ የዘመናዊ ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚነት መጠን እያደገ የመጣ ቢሆንም መጠኑ በሚፈለገው ደረጃ ላይ እንደማይገኝ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።  

የኢትዮጵያ መንግስትም የዜጎችን የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማጠናከር የሚያስችል ስትራቴጂ ቀይሶ እየሰራ መሆኑን ነው ብሄራዊ ባንክ ያስታውቃል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም