ዶክተር ወርቅነህ በስካንዲኔቪያ አገራት የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዶክተር ወርቅነህ በስካንዲኔቪያ አገራት የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 29/2010 በስካንዲኔቪያ አገራት የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ዛሬ ወደ ዴንማርክ ኮፐንሀገን በማምራት ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ። ዶክተር ወርቅነህ ባለፉት ሁለት ቀናት ወደ ኖርዌይ እና ፊንላንድ በመጓዝ ከአገራቱ ባለስልጣናት ጋር በወቅታዊ አገራዊ፣ አካባቢያዊና ዓለም ዓቀፋዊ የጸጥታና የልማት ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል። በዴንማርክ ቆይታቸውም ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ላርስ ሎኬ ራሙሰን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንደርስ ሳሙዬልሰን እንዲሁም ከአገሪቱ ፓርላማ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ጋር በሁለትዮሽ፣ በአካባቢያዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ አስታውቋል። ዴንማርክ ባላት የልማት ትብብር አማካኝነት ለኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ እያደገ መምጣቱን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አመልክቷል። ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ኢትዮጵያን የስትራቴጂክ አጋር አድርጋ የምትቆጥረው ዴንማርክ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2004 ከአገሪቱ ጋር በፈጠረችው የልማት ትብብር ግብርና፣ ድህነት ቅነሳ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ በሃይልና በትምህርት ዘርፎች በዋነኛነት ድጋፍ በማድረግ ላይ ትገኛለች። የዴንማርክ መንግስት ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ባደረገው ስምምነት 100 ሜጋ ዋት ያመነጫል ለተባለው የአሰላ የንፋስ ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት የሚውል 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መስጠቱ የሚታወስ ነው። ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮኑ በእርዳታ የተሰጠ ሲሆን ቀሪው በአነስተኛ የወለድ መጠን የሚከፈል ብድር ነው። ኢትዮጵያና ዴንማርክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1960ዎቹ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ዴንማርክ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2004 የከፈተች ሲሆን ኢትዮጵያ በዴንማርክ ርዕሰ መዲና ኮፐንሀገን የቆንጽላ ጽህፈት ቤት አላት። ኢትዮጵያ ከዴንማርክ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የምታከናውነው ለንደን በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ነው።