ቀጥታ፡

ለተፈናቀሉ ወገኖች ለህክምና አገልግሎት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል

ግንቦት 6/2011በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ለተፈናቀሉ ወገኖች ለህክምና አገልግሎት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፈው አንድ አመት ለተፈናቃይ ወገኖች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ከ600 ሚሊዮን  ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።

ወጭው በገንዘብ  የማይተመኑ የህክምና አገልግሎቶችን ያላካተተና በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብቻ የተደረገ ሲሆን ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች የወጣውን ጨምሮ ከፍተኛ ነውም ብለዋል።

የመተንፈሻ አካላት ችግር፣ የአይን ህመም፣ እከክ፣ ተቅማጥ፣ የሆድ ትላትልና የሳንባ  ምች በብዛት የታዩ በሽታዎች ናቸው ተብሏል።

ባለፉት ሶስት ሳምንታት በአማራ፣ ትግራይ፣ ሶማሌ፣ ሃረሪ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በሚገኙ 76 ወረዳዎች ከ38 ሺህ በላይ ሰዎች የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን  ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት 205 የጤና ባለሙያዎች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ባለፉት ስድስት  ሳምንታት ብቻ ለመድሃኒትና መድሃኒት ግብአቶች እንዲሁም ለሰው ሃይል ምደባ ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል ብለዋል።

እንደ ዶክተር በየነ ገለጻ በአማራ፣ ደቡብ፣ ሶማሊያና ኦሮሚያ ክልሎች ከ14 ሺህ  በላይ እድሚያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት ከምግብ እጥረት ጋር በተገናኘ ለገጠማቸው ህመም ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል።

በተመሳሳይ ከ13 ሺህ በላይ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶች በምግብ እጥረት ሳቢያ  ለገጠማቸው የጤና እክል ህክምና እንደተደረገላቸው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የቅድመ መከላከልና መሰረተ ልማቶች ላይ በትኩረት በመስራት ችግሩ ከተከሰተ በኋላ እየወጣ ያለውን ከፍተኛ ወጪ ማስቀረት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በመጪው የመኸር ወቅት በጎርፍና ሌሎች ከክረምት ጋር ተያይዞ የሚመጡ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከልና በሰው ጤና ላይ የሚደርስውን ጉዳት ለማስቀረትና ወጪን ለመቀነስ መስራት እንደሚያስፈግልም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም