በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች ከ170 በላይ ሰዎች በአተት በሽታ ተይዘዋል የሚል ጥርጣሬ አሳድሯል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች ከ170 በላይ ሰዎች በአተት በሽታ ተይዘዋል የሚል ጥርጣሬ አሳድሯል
አዲስ አበባ ግንቦት 6/2011 በአማራ ክልል በሁለት ዞኖች ተከስቷል በተባለው የአተት በሽታ 174 ሰዎች ተይዘዋል የሚል ጥርጣሬ መኖሩን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ የወረርሽኙን መከሰት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በክልሉ በዋግህምራ ዞን አበርጌሌ ወረዳ 61 ሰዎች፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ 110 ሰዎች እንዲሁም በበየዳ ወረዳ 4 ሰዎች በወረርሽኙ ተይዘዋል የሚል ጥርጣሬ አሳድሯል።
በክልሉ ሁለቱ ዞኖች ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ 174 ሰዎች በበሽታው ሳይያዙ አይቀሩም የሚል ጥርጣሬ አለ።
እንደ ምክትል ዳሬክተሩ ገለፃ በበየዳ ወረዳ የተከሰተው የአተት ወረርሽኝ መሆኑን ለማረጋገጥ በማጣራት ላይ ነው።
ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች የወረርሽኙን መንስኤ ለማጣራትና ለተጠርጣሪዎቸ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ወደ ስፍራው ተጉዘዋል።
በተጨማሪም ከአለም የጤ ድርጅትና ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን በቦታው በመገኘት የመድሃኒት፣ የህክምና ግብአትና መሳሪያዎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የተጠረጠሩ ሰዎችን ለይቶ ለማከም በጠለምትና አበርጌሌ ወረዳዎች ለይቶ ማከሚያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ከተጠቀሱት ወረዳዎች ውጪ አጎራባች በሆኑ የአማራና ትግራይ ክልል ወረዳዎች በሽታው በቀላሉ ሊዛመት ስለሚችል የቅኝት ስራ እየተሰራ ነው።
ወረርሽኙ ቢስፋፋ የመድሃኒት፣ የህክምና መሳሪያና ግብአት እንዲሁም በሰው ሃይል አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የአተት በሽታ ምልክት በታየባቸው አካባቢዎች የመንገድና የስልክ ኔትወርክ አለመኖር ችግር እንደሆነባቸውም ምክትል ዳሬክተሩ አብራርተዋል።
ወረርሽኙ የተከሰተበት ቦታ ለመድረስ በእግር እስከ 6 ሰአት እንደሚወስድ ገልጸው በድሃኒትና ባለሙያዎችን ወደ ቦታው ለማድረስ መቸገራቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና እንዳይስፋፋ ለመከላከል አጣዳፊ ተቅማጥና ተውከት የታየባቸው ሰዎችን የቤት ለቤት ቅኝት ይደረጋልም ብለዋል።
የአተት በሽታን ከሚያመጡ አንዱ ኮሌራ ሲሆን የተከሰተው ወረርሽኝ ኮሌራ መሆኑ በምርመራ በማረጋገጥ ከአለም የጤና ድርጅት ጋር በመተባባር ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ አካባዎች በቀጣይ ሳምንት ክትባቱ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
በበሽታው የተጠረጠሩ ቤተሰቦችና ቅርብ ግንኙነት ለነበራቸው ሰዎች የውሃ ማከሚያ መድሃኒት መስጠትና በማስተማር በሽታው እንዳይስፋፋ ይሰራል ተብሏል።
በሶማሊያና ኬንያ የተከሰተው የኮሌራ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይዛመት ለሁለቱ አገሮች አጎራባች የሆኑ የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች ወረዳዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ያለው የንጹህ ውሃ አቅርቦት ችግር የአተት በሽታ ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ መደረግ አለበትም ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች የአተት ወረርሽኝ መከሰቱን ከሳምንት በፊት መግለጹ ይታወሳል።