የፍሳሽ ማስወገጃ ጣቢያዎች በአጠቃቀም ጉድለትና በስርቆት ጉዳት እየደረሰባቸው ነው

85

ግንቦት  6/2011 በአዲስ አበባ በቅርቡ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ጣቢያዎች በአጠቃቀም ጉድለትና በስርቆት ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን የከተማው የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋለም ባዩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት  ከተገነቡበት ዓላማ ውጪ ድንጋይ፣ አሸዋ፣ ቤንዚን፣ ናፍጣና ሌሎች ከኢንዱሰትሪ የሚለቀቁ ተረፈ ምርቶችንና የጎርፍ ውሃ ማስወገጃ መስመሮችን የፍሳሽ ማስወገጃ ጣቢያዎቹ ጋር በማያያዝ ይለቀቃሉ።

በተጨማሪም የፍሳሽ ማስወገጃ የብረት ክዳኖች በህገ-ወጦች በመዘረፋቸው ጎርፍና ሌሎች ባዕድ ነገሮች በመስመሩ በመግባት መውረጃዎቹን እያስተገጓጎሉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሁለት ቢሊዮን ብር ተገንበቶ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ወደ ስራ የገባው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ባለፈው የበልግ ወር በጣለው ዝናብ ከፍተኛ የጎርፍ  አደጋ እንደደረሰበትም  አስታውሰዋል።


በፍሳሽ ማጣሪያው ላይ የገባው ጎርፍና  ባዕድ ነገር የማጣሪያ ጣቢያውን የተለያዩ ክፍሎች እንዲሁም በባይሎጂካል የማጣሪያ ክፍሉ ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ይህንን ተረድቶ የፍሳሽ ማስወገጃዎች  መስመሮችን ከመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ ውጪ ለሌሎች ግልጋሎቶች አለማዋልና በመስመሩ ክዳን ላይ የሚደርሰውን ህገ-ወጥ ዘረፋ የሚያካሂዱትን ለሚመለከተው እንዲጠቁም ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በፍሳሽ መስወገጃዎች ውስጥ ሌሎች ባዕድ ነገሮችን ባለመጨመር ህብረተሰቡ እንዲተባበር አቶ ተስፋለም ተናግረዋል።

በተለይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ወጥቶባቸው  የተገነቡ የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ከአዳጋና ከብልሽት በመጠበቅ ከተማውን ጽዱ ለማድረግ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በከተማው በቅርቡ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ያለው  የቃሊቲ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ  በሰባት ክፍለ ከተማ የሚገኙ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም አውስተዋል።

ማጣሪያ ጣቢያው በቀን 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ  ፍሳሽ ቆሻሻን ማጣራት የሚችል ሲሆን በተለያዩ የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይቶች ላይ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያዎች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

በምስራቁ የከተማዋ አካባቢዎችና አቃቂን ጨምሮ ሶስት ከፍለ ከተሞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመናዊ የፍሳሽ  ማስወገጃ ጣቢያዎች በመገንባት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም