ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ኬኒያ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ኬኒያ ገቡ
ግንቦት 6/2011 ፕሬዝዳንቷ ዛሬ ናይሮቢ ጆሞ ኬኒያታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማ፣ በኬኒያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በቆይታቸው ከኬኒያ አቻቸው ኡሁሩ ኬኒያታ ጋር በሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ የካቲት 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የሁለቱን እህትማማች አገራት ወዳጅነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ጋር መምከራቸው ይታወሳል።
የአሁኑ የፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ጉብኝትም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የቆየውን የኢትዮጵያና ኬኒያ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያና ኬኒያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1954 ነው።
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1965 ኤምባሲዋን በኬኒያ ስትከፍት፤ ኬኒያ ደግሞ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1967 በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከፍታለች።