ቢሾፍቱ ስምንቱ ኃይቆቿ ከፍተኛ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ምንጭ ሆነዋታል

ግንቦት 6/2011ስምንቱ የቢሾፍቱ ሐይቆች የቢሊዮን ብር የኢንቨሰትመንት ምንጮች ፣ የቱሪዝም መስህቦቸና የውበት መገለጫዎች ሆነው እያገለገሉ እንደሚገኙ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ ።

የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መርድ አስፋው ለኢዜአ እንደገለፁት ከተማዋ የሰባት የተፈጥሮ ሐይቆችና የአንድ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ባለቤት ናት ።

የተፈጥሮ ሐይቆቹ ኩሪፍቱ ፣ ቢሾፍቱ ፣ ባቦጋያ ፣ ሆራ አርሰዲ ፣ መገሪሳ ፣ ኪሎሌና ጨለለቃ በሚል ስያሜ ሲጠሩ ሰው ሰራሽ ሐይቁ ደግሞ በልበላ ሐይቅ በሚል ስም ይታወቃል።

ክረምት ብቅ እያለ በበጋ ወራት አልፎ አልፎ ከሚደርቀው የጨለለቃ ሐይቅ በስተቀር ቀሪዎቹ በስፋታቸውም ሆነ በጥልቀታቸው የሚታወቁና የሽርሽር ጀልባዎች ጭምር በብዛት የሚንቀሳቀሱባቸው ትላልቅ ሐይቆች ናቸው ።

“በከተማዋ 8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው 431 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው አብዛኛዎቹ ወደ ስራ ገብተዋል” ብለዋል ።

ከባለሃብቶቹ መካከል 25 በመቶ የሚሆነው ካፒታላቸው በሀይቆቹ ዙሪያ ትላልቅ ዘመናዊ ሆቴሎችና ማራኪ ሪሶርቶች በመገንባት ኢንቨስት ያደረጉ ናቸው ብለዋል ።

ለአብነትም በቢሾፍቱ ሃይቅ ዳርቻ ያሉት ድሪምላንድና ፒራሚድ ሆቴሎች ፣ በባቦጋያና በኩሪፍቱ ሃይቆች ዙሪያ የተገነቡት ማርካን ፣ ኩሪፍቱ ፣ ባቦጋያ ፣ ሊሳክ ፣ ፔሊካንና፣ አዱላላ የመሳሰሉ ሪሶርቶች ይታወቃሉ ።

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ባለሃብቶች በሃይቆቹ ዙሪያ ቦታ ወስደው በአገልግሎት ዘርፍ ግንባታዎች ለማካሔድ መጠየቃቸውን አቶ መርድ ተናግረዋል ።

ሐይቆቹ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታቸው ባሻገር ለከተማዋ ውበትና ለኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ ትሰስር መጠናከር ገንቢ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን በመግለፅ የኢሬቻ በዓል በድምቀት የሚከበርበትን የሆራ አርሰዲ ሐይቅ ለአብነት አንስተዋል ።

የቢሾፍቱ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት የሆቴሎችና ሬስቶራንቶች የብቃት ማረጋገጫ የስራ ሒደት ባለሙያ አቶ በቃሉ ፉፋ እንደገለፁት ወደ ከተማዋ የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ በመምጣቱ አምና ከዘርፉ 270 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል ።

ከዚህ ውስጥም ወደ 92 ሚሊዮን ብር የሚጠጋው ገንዘብ የተገኘው ከውጭ ሃገራት ዜጎች መሆኑንም አስረድተዋል።

በዚህም 252 ሺህ በላይ የሃገር ውስጥ ጎበኚዎች ሐይቆቹን ጨምሮ የከተማዋ አረንጓዴ አካባቢዎች ተዟዙረው መጎብኘታቸውን አቶ በቃሉ ተናግረዋል ።

በ2010 ዓ.ም ከተማዋን የጎበኙ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር ከ2006 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር ከ260 ሺህ ወደ 343 ሺህ 861 ያደገ ሲሆን በገቢ ደረጃ ደግሞ ከአራት እጥፍ በላይ ብልጫ ማሳየቱን ከከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

ለእድገቱ ዋናው ምክንያት ደግሞ የሐይቆቹን ተፈጥሮአዊ ውበትና ሐይቆቹን ተከትለው የተገነቡ የመዝናኛ ማእከላት ቁጥር እየጨመሩ በመምጣታቸው ነው ተብሏል ።

በሀይቆቹ ዙሪያ በአገልግሎት ዘርፍ ከተቋቋሙት ተቋማት መካከል የአዱላላ ሪዞርት የኢቨንትስ ክፍል ሃላፊ አቶ ፋንታሁን ንዋይ በሰጡት አስተያየት ሀይቆቹ የመዝናኛ ማእከላቱ እስትንፋስ በመሆናቸው ተገቢው ጥበቃና እንክብካቤ ይደረግላቸዋል ።

የሊሳክ ሪሶርት ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ጌታሁን በሰጡት አስተያየት ደግሞ እሳቸው የሚመሩትን ሪዞርት ህልውና ከሐይቁ ነጥሎ ማየት ስለማይቻል ለሀይቁ ተገቢውን ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ።

የከተማው አስተዳደር ከሐይቁ በሞተር እየተሳበ ለተለያዩ ስራዎች የሚወሰድ ውሃ እንዲከለከል በማድረግ ጭምር ቁጥጥር መጀመሩን በመልካም ጎኑ ያነሱት አቶ ሳሙኤል ሐይቁን ተከትለው ወደ ስራ የገቡ ተቋማት ለራሳቸው ሲሉ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም