በሐዋሳ ዘመናዊ የጎርፍ ማፋሰሻ ግንባታ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐዋሳ ዘመናዊ የጎርፍ ማፋሰሻ ግንባታ እየተከናወነ ነው
ሐዋሳ ግንቦት6 /ቀን 2011 የሐዋሳ ከተማን ከጎርፍ ስጋት ለመከላከል ከ93 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ዘመናዊ የጎርፍ ማፋሰሻ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ገለጸ፡፡
ነዋሪዎቹ ሥራው የጎርፍ ስጋታችንን ቀንሶታል ብለዋል፡፡
የማዘጋጃ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሩ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተማዋን ከጎርፍ ስጋት ነጻ ለማድረግ በጥናት የተደገፈ ዘመናዊ የጎርፍ ማፋሰሻ ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡
ቀጣዮቹን 20 ዓመታትን ታሳቢ ያደረገው ግንባታ በስምንት ቦታዎች የሚከናወን ሲሆን፣ አምስቱ በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቁ ገልጸዋል።
በከተማዋ የሚገኙ ሁለት ተራራዎችን መነሻ ያደረገውና መዳረሻው የሃዋሳ ሃይቅ የሆነው ግንባታ እርስ በርስ የተገናኘና ወደ ሃይቁ የሚገባውን ጎርፍ የሚያጣራ ሰው ሰራሽ ማጣሪያ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡
በዚህ ዓመት ለማከናወን ከተያዘው ሥራ 70 ከመቶ የተጠናቀቀው ግንባታ የነባር ማፋሰሻዎችን ጥልቀት ማሳደግና በጥናቱ የተለዩ ሶስት ማፋሰሻዎች ግንባታን ያካትታል፡፡
ከዚህ በኋላ በከተማው የሚሰሩ መንገዶች የጎርፍ ማፋሰሻዎችን መሠረት ባደረገ መልኩ እንዲገነቡ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል፡፡
ከግንባታው ጎን ለጎን ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ ጽዳትና ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ለማጠናከር እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ግንባታው የስጋት ቀጠና በሆኑ አካባቢዎች ለውጥ ማምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የማዘጋጃ ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሻለ ዎንቴ ናቸው፡፡
አዲሱ ማረሚያ ቤት፣ ዩኒቨርሲቲና ቃለህይወት ቤተክርሲቲያን አካባቢዎችን ለአብነት አንስተው በከፍተኛ ሁኔታ ጎርፍ በሚተኛበት አሮጌው አየር ማረፊያም 12 ሜትር ጥልቀት ያለው ውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ/ፖንድ/ እየተቆረፈ ነው ብለዋል፡፡
በዘመናዊ መልክ የሚገነባው የጎርፍ ማጠራቀሚያ እንደ ውሃ ባንክ በማገልገል ለከተማ ግብርና የሚረዳ ሲሆን፣ ወደ ሃይቅ የሚገባውን ደለል በማሰቀረት ለሌላ አገልግሎት ለማዋል እንደሚያስችል አመልክተዋል ፡፡
በቡልቻ መንደር የጢልቴ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አገኘሁ ገቢሳ አካባቢያቸው ከአላሙራ ተራራ በሚወርደው ጎርፍ ምክንያት በስጋት ይኖሩ እንደነበር አስታውሰው፣የጎርፍ ማፋሰሻው ስጋቱን እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል፡፡
ማፋሰሻዎቹ የረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ኅብረተሰቡን እንደሚያስተባብሩ ተናግረዋል፡፡
ማፋሰሻ ቦዮች በነበራቸው ጥበት ምክንያት ጎርፍ አስፋልቱን ስለሚያጥለቀልቅ ለእንቅስቃሴያቸው ይቸገሩ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የሾራና ቅልጦ መንደር አስተባባሪ አቶ በቀለ ገብረመድህን ናቸው፡፡
ነዋሪዎችሥራውን በማገዝ በየሳምንቱ አካባቢያቸውንና ቦዮችን በማጽዳት ድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ የሚገነባውዘመናዊ የጎርፍ ማፋሰሻ ሲጠናቀቅ ከተማዋን ከጎርፍ ስጋት እንደሚያወጣት ከማዘጋጃ ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡