ቀጥታ፡

የክለቦች የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ተጀመረ

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2011 ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ የክለቦች የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተጀመረ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ኤሌትሪክ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ፣ ማማስ ኪችን፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ እና የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) በሻምፒዮናው ላይ በሁለቱም ጾታዎች የሚሳተፉ ክለቦች ናቸው።

በሻምፒዮናው ላይ 46 ወንድና 34 ሴት በድምሩ 80 ስፖርተኞች ተሳታፊ ናቸው።

በሁለቱም ጾታዎች በነጠላ፣ በጥንድ ( ወንድ እና ወንድ )፣ በድብልቅ (ወንድና ሴት) እና የቡድን የዙር ውድድር ሻምፒዮናው የሚካሄድባቸው ዘርፎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ አበባ አማረ ለኢዜአ እንደገለጹት የሻምፒዮናው አላማ በስፖርቱ ብቃት ያላቸውን ተወዳዳሪዎች ለማፍራትና በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያን የሚውክሉ ስፖርተኞችን ከወዲሁ ለመመልመል ነው።

ለክለቦችም የውድድር እድል ለማስፋት እንዲሁም ስፖርቱን ለማስተዋወቅና ተቀባይነቱ እንዲያደድግ የሻምፒዮናው መዘጋጀት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

በአጠቃላይ በሻምፒዮናው የሚያሸንፈው ክለብ ከሐምሌ 24 እስከ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በናይጄሪያ ሌጎስ ከተማ በሚካሄደው 25ኛው የአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክሎ እንደሚሳተፍም ጠቁመዋል።

ዛሬ በሻምፒዮናው መክፈቻ ቀን በተደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች በታዳጊ ወንዶች የቡድን የዙር ውድድር ኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናያዊ ማህበርን 3 ለ 0 ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚን በተመሳሳይ 3 ለ 0 ረቷል።

በታዳጊ ሴቶች የቡድን የዙር ውድድር የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ኢትዮ-ኤሌትሪክን 3 ለ 0 አሸንፏል።

የማጣሪያ ጨዋታዎች በነገው ዕለትም ይቀጥላሉ።

የ2011 ዓ.ም ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ሻምፒዮና እስከ ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

ከጥር 27 እስከ የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም በጅማ ከተማ በተካሄደው የ2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ አሸናፊ ነበር።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ውሃ ዋና የክልሎችና የክለቦች ሻምፒዮና ከግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በቢሾፍቱ መኮንኖች ክበብ ዛሬ ተጀምሯል።

ኦሮሚያ ፣ ደቡብ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች  የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ እና ቢሾፍቱ የውሃ ዋና ስፖርት ክለቦች በሻምፒዮናው ላይ ተሳታፊ ናቸው።

የክለቦች እና የክልሎች ውድድር በተናጠል ሲካሄዱ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱንም በማጣመር ሻምፒዮና መዘጋጀቱን ከኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እርስ በእርሳቸው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ፣ የክለቦችን ተሳትፎ መጨመርና ክለቦችን ማጠናከር፣ በ2011 ዓ.ም መጨረሻ እና በ2012 ዓ.ም በሚካሄዱ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመመልመልና ለመመምረጥ እንዲሁም ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሻምፒዮናው አላማዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ውሃ ዋና የክልሎችና የክለቦች ሻምፒዮና እስከ ግንቦት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም