ቀጥታ፡

የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ተቻችሎ በመኖርና ለሰላም በሚያበረክተው ልክ ትኩረት አላገኘም--ምሁራን

ባህርዳር ግንቦት 5 /2011 የስፖርት ሳይንስ ትምህርት የሕዝቦችን ተቻችሎ የመኖርና ለሰላም የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ያህል ትኩረት እንዳላገኘ የዘርፉ ምሁራን አመለከቱ።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ያዘጋጁት አራተኛው አገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ውይይት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  የልዩ ፍላጎት ትምህርቶች  የጥናትና ጥራት ያለው ትምህርት  ፍኖተ ካርታ መሪ  ሎሬት ፕሮፐፌሰር  ጥሩሰው ተፈራ በውይይቱ ላይ  እንደገለጹት  የስፖርት ሳይንስ ትምህርት አካላዊ ብቃትና ጤንነትን ለመጠበቅ ካለው ድርሻ ሊጤን ይገባዋል።

ለትምህርቱ ግብአቶች ያለማሟላታቸው ሳያንስ ዘርፉን የአንደኛ ደረጃ  ሥርዓተ ትምህርት  አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ ባለድርሻ አካላት መቀየር አለባቸው ብለዋል።

መንግሥት በአካልና በአዕምሮው የዳበረ ዜጎችን ለመፍጠር ብሎም ሰላማዊ ግንኙነትን ለመፍጠር ያለውን ድርሻ ከግምት አስገብቶ እንዲሰራበትም ጠይቀዋል።

ዘርፉ የሚያበረክተውን  አስተዋጽኦ ከግምት ያስገባ  አደረጃጀትና በጀት በመመደብ  ማስፋፋት ለሁለንተናዊ እድገት ያለውን ድርሻ እንደሚያሳድገውም ፕሮፌሰር ጥሩሰው አመልክተዋል።

“ዓለም ስፖርትን የሰላምና አብሮነትን መስበኪያ ከማድረግ በተጨማሪ  የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እያደረገው ነው።በኢትዮጵያም የህዝቦችን አብሮነት ለማጠናከርና  በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ትውልድን ለመቅረጽ ለስፖርት ሳይንስ ትምህርት መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል።

ስፖርት ለሕዝቦች ግንኙነት ያለውን ድርሻ የሚያሳይ ጥናት በማቅረብ ምሁራን ድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተወካይ ወይዘሮ ሄሮዳዊት ዘለቀ ናቸው።

በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እምቅ የተማረ ሃይልን በመጠቀም የኦሊምፒክ መርሆዎችን ለማስፋፋትና ከዩኒቨርሲቲዎች የጋራ እቅድ በማውጣትና አምባሳደሮችን ለመሾም ዝግጅቱ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የስፖርት ሳይንስ ትምህርት በመቻቻል የሚያምን ዜጋን ለማፍራትና  ሚዛናዊ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ ለመቅረጽ ባለው  ድርሻ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት አካዳሚ ዲን ዶክተር ተስፋዬ  ደሳለኝ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው በአገር ደረጃ በትምህርቱ ላይ የሚታዩትን ተግዳሮቶችን ለማወቅና መፍትሄ ለማፈላለግ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ሊታገዝ  ይገባል ብለዋል።

 በውይይቱ ላይም የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም