አርሶ አደሮች ከነጭ ሽንኩርት ምርት ከ250 ሺህ ብር በላይ ገቢ አገኙ - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሮች ከነጭ ሽንኩርት ምርት ከ250 ሺህ ብር በላይ ገቢ አገኙ
ጎንደር ግንቦት 5/2011 በመስኖ ካለሙት የነጭ ሽንኩርት ምርት ከ250 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን የጎንደር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
ከወረዳው 540 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለገበያ መቅረቡን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የወረዳው አርሶ አደሮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት በተያዘው ዓመት በመስኖ ካለሙት ምርት ገቢውን አግኝተዋል።
በወረዳው የጭንጫዬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መከተ ባዬ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ባለሙት 80 ኩንታል አምርተው160 ሺህ ብር ገቢ አግኝቼያለሁ ብለዋል።
በወረዳው የደጎላ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ግዛው ዳምጤ ዘንድሮ አንዱን ኪሎ ከ18 እስከ 20 ብር በመሸጥ 80 ሺህ ብር ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በገቢ ኑሮአቸውን ማሻሻላቸውን ገልጸዋል።
"በመስኖ የሚለማ ነጭ ሽንኩርት በጥራትም ሆነ በምርታማነት ከፍ ያለ ነው" ያሉት አርሶ አደሩ፣ዘንድሮ በሩብ ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ነጭ ሽንኩርት 40 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
በአንድ ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ካለሙት ነጭ ሽንኩርት 125 ኩንታል ማምረታቸውን በወረዳው የጭህራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሹመት መልኬ ገልጸዋል።
ካመረቱት የነጭ ሽንኩርት ምርት 250 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባይለየኝ አድማሱ በወረዳው በነጭ ሽንኩርት የመስኖ ልማት ከ16 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።
በዘንድሮ ዓመት የበጋ መስኖ ልማት ከ4 ሺህ ሄክታር መሬት በነጭ ሽንኩርት መልማቱን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ከዚህም 542 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ምርቱ የነበረው ዋጋ አምራች አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዳላደረጋቸው አስታውሰዋል።
ዘንድሮው የተመረተው ምርት ጎንደርን ጨምሮ ወደ ባህርዳርና አዲስ አበባ ከተሞች በመላኩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ኃላፊው አስረድተዋል።
በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በነጭ ሽንኩርት የሚለማ ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መኖሩን ከወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።