በጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መስመር ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ ነው

93
አዲስ አበባ ሚያዚያ 22/2010 በጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የማስተላለፊያ መስመር ላይ በብሬከር መክፈት ምክንያት ባጋጠመ ችግር የተፈጠረውን የኤሌትሪክ ኃይል መቋረጥ ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል የውጭ ግንኙት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት ዛሬ ማምሻውን በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የኤሌትሪክ ኃይል ተቋርጧል። ለመቋረጡ ምክንያት የሆነው የጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የማስተላለፊያ መስመር የሚከፍተውና የሚዘጋው 'ብሬከር' በመከፈቱ የተፈጠረ ችግር ነው። ከ1 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌትሪክ ኃይል የሚያመርተው ጊቤ 3 የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ በአሁኑ ሰዓት ትልቁ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ነው። ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በአገሪቷ ባሉ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ የሃይል ማስተላለፊያዎች ድረስ የተሳሰረ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ምስክር፤ በማመንጫው በሚደርስ ማንኛውም ችግር "በሌሎቹ ላይ ተጽእኖ ስለሚፈጥርና መቋቋም ስለማይችሉ መብራት መቋረጡን ነው" ያብራሩት። ችግሩ ተፈቶ ወደ መደበኛው ስርጭት ለመመለስ "ከብሄራዊ የኤሌትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ ጣቢያ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ሙያተኞች ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን" ተናግረዋል። ኅብረተሰቡም በትዕግስት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም