ቀጥታ፡

ጎንደር ከተማ በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ድሉን አስመዘገበ

ግንቦት 3/ 2011 ጎንደር ከተማ በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ድሉን አስመዘገበ።

በፕሪሚየር ሊጉ 11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ተደርገዋል።
በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ እንግዳው ክለብ ጎንደር ከተማ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 20 ለ 18 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ድሉን አስመዝግቧል።

በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አዲስ ተሳታፊ የሆነው ጎንደር ከተማ ከዛሬው ጨዋታ በፊት ያደረጋቸውን 10 ጨዋታዎች የተሸነፈ ሲሆን የዛሬውን ተከትሎ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል።

የሁለተኛው ዙር የፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ከተጀመረ ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፈው ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በ7 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ሌላ ጨዋታ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መከላከያን 34 ለ 22 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የዛሬውን ጨምሮ እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጋቸውን 11 ጨዋታዎች በማሸነፍ ስኬታማ ጉዞ እያደረገ ይገኛል።

ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ በ10 ነጥብ በነበረበት አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በክልል ከተማ ዱራሜ ላይ ፌዴራል ፖሊስ ከምባታ ዱራሜን 31 ለ 30 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ውጤቱንም ተከትሎ ፌዴራል ፖሊስ በ14 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ከምባታ ዱራሜ በ10 ነጥብ በነበረበት ስድስተኛ ደረጃ ረግቷል።

የ11ኛ ሳምንት የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል።

በዚሁ መሰረት ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር መመሪያ መሰረት አንድ ክለብ ሲያሸነፍ ሁለት ነጥብ የሚያገኝ ሲሆን አቻ ሲወጣ ደግሞ አንድ ነጥብ የሚያገኝ ይሆናል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ22 ነጥብ ሲመራ፣ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ17 መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ15 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ የመጀመሪያ ድሉን ያስመዘገበው ጎንደር ከተማ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃን ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም