ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በኬኒያ የስራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በኬኒያ የስራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2011ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኬኒያ የአንድ ቀን የስራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።
ፕሬዚዳንቷ በኬንያ ቆይታቸው ከኬኒያ አቻቸው ኡሁሩ ኬኒያታ ጋር በሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ አለም ለኢዜአ አስታውቀዋል።
ኡሁሩ ኬኒያታ የካቲት 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የሁለቱን እህትማማች አገራት ወዳጅነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጋር መምከራቸው ይታወቃል።
የአሁኑ ጉብኝትም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የቆየውን ጠንካራና የማይዋዥቅ የኢትዮጵያና ኬኒያ ግነኙነት የበለጠ ያጠናክረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አምባሳደር መለስ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ኬኒያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1954 ነው።
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1965 ኤምባሲዋን በኬኒያ የከፈተች ሲሆን ኬኒያ ደግሞ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1967 በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከፍታለች።
የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ግንቦት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በኬንያ የአንድ ቀን የስራ ጉበኝት ያደርጋሉ።