የ68ኛው ዓመት የኮሪያ ዘመቻ መታሰቢያ በዓል ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
የ68ኛው ዓመት የኮሪያ ዘመቻ መታሰቢያ በዓል ተከበረ
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2011 የ68ኛው ዓመት የኮሪያ ዘመቻ መታሰቢያ በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያንና በኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ ተከበረ።
በእለቱ በተከናወነው የጸሎትና የተለያዩ መርሃ ግብሮች ላይ የኮሪያ ዘማቾች ማህበር፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ በወቅቱ ጦራቸውን ወደ ደቡብ ኮሪያ የላኩ መንግስታት አምባሳደሮች ወታደራዊ አታሼዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች፣ ከአዲስ አበባና ከክልሎች የመጡ አርበኞች ተሳትፈዋል።
በኮሪያ ልሳነ ምድር ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት የተባበሩት መንግስታት ደርጅት በቻርተሩ መሰረት ለኢትዮጵያ ጥሪ ሲያደርግላት ወዲያውኑ ተቀብላ ወታደሮቿን ወደ ስፍራው አዝምታለች።
በወቅቱም ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መጠበቅ ያላትን ፅኑ ፍላጎትና ለገባችው ቃል ኪዳን ታማኝነቷን ያሰያችበትና ያሰመሰከረችበት ወቅት እንደነበረ ነው የኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማቾች ማህበር ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ ባደረጉት ንግግር ያወሱት።
የኮሪያ ዘማቾች ያስመዘገቡት አኩሪ ታሪክ ሊረሳ የማይችል መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በታሪክ ሲታወስና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ አኩሪ ታሪክ መሆኑን ተናግረዋል።
ታሪኩ የበለጠ እንዲታወቅና ትውልድ እንዲማርበት በወቅቱ የነበሩ ቅርሳ ቅርስ በአግባቡ ለማስተዳደር እንዲቻል ወጣቱ ትውልድ እንዲረከብ ጥሪ አቅርበዋል።
"ሰላም ቃሉ ሶስት ፊደል ብቻ ያለው ተክል፤ ፍሬዋ ግን ቁጥር እንደማይገድበው ተገንዝቦ በአገሪቷ ሰላምን ለማስፈን ወጣቱ ትውልድ መረባረብ ይኖርበታል" ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ሊም ሁንሚን በበኩላቸው፤ ከ68 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮች በኮሪያ ልሳነ ምድር ለኮሪያ ሰላምና ነፃነት ላበረከቱት አስተዋጾኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በአሁኑ ወቅት ኮሪያ የዳበረ ዴሞክራሲና ጠንካራ የኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗን ያመለከቱት አምባሳደሩ፤ እዚህ ለመድረስ አትዮጵያን ጨምሮ የዓለም ሰላም አስከባሪዎች መስዋዕትነት መክፈላቸውን አውስተዋል።
የኮሪያ ዘማቾች የምን ጊዜም የኮሪያና የህዝቦቿ ጀግና መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የሁለቱ አገሮች ትብብርና ትስስር የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የዓለም አቀፍ የኮሪያ ዘማቾችን ወክለው ንግግር ያደረገት በኢትዮጵያ የቱሪክ አምባሳደር ያፕላክ አልፕ በበኩላቸው፤ ዘመቻው አገሮችን በአንድ ማስተሳሰር የቻለና ትምህርት ሊወሰድበት የሚገባ ነው። በቀጣይም የነጻነት ተምሳሌት ይሆናል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ፣ የአሜሪካ፣ እስያና ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አምባሳደር ማህሌት ሀይሉ ደግሞ፤ የኢትዮጵያና ኮሪያ ግንኙነት ጠንካራ፣ የአብሮነታቸውም ከልብ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅትም አገሮቹ በትምህርት፣ በአቅም ግንባታ፣ በልምድ ልውውጥ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስክ እየተጠናከረ መምጣቱን አብራርተዋል።
በቀጣይም የኮሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የኢንቨሰትመነት ተሳትፎ እንዲጎለብትና እንዲያድግ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
ኢትዮጵያ በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ያለው የጦርነት ውጥረት በውይይት እንዲፈታና በኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላም እንዲሰፍን የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በኮሪያ ዘመቻ ወቅት ስድስት ሺህ ሰራዊት ያሳተፈች ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 122 ህይወታቸውን ሰውተዋል። የተቀሩት ደግሞ ወደ አገራቸው በጀግነነት ተመልሰዋል። በወቅቱ የተሰዉ ጀግኖች አጽም በኢትዮጵያ በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በክብር አርፏል።