በትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ በ10 ቢሊዮን ብር ልዩ የሆነ ሪዞርት ሊገነባ ነው

ግንቦት 3/ 2011በትግራይ ክልል በውቅሮ ከተማ ከ10 ቢልዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የቱሪስት ማረፊያ ሪዞርትና ሆቴል ግንባታ ተጀመረ።

በውቅሮ ከተማ እንዲገነባ የተመረጠበት ምክንያት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ስልጣኔ እና ታሪካዊ አመጣጥ የሚገልፁ የሳባውያን እና አክሱማውያን ታሪካዊ ስፍራዎች በብዛት ስለሚገኙበት እንደሆነ ተገልጿል።

ሳባዊ ሪዞርት በመባል የተሰየመው የቱሪስት ማረፈያ ፕሮጀክት አጠቃላይ ግንባታ በአምስት ምዕራፍ ተከፋፈሎ የሚከናወን ነው።

የአረንጓዴ ፓርክ፤መዋኛና የሰርገኞች መዝናኛ፤የኮንሰርት ዝግጅት አዳራሾች፤ የቤት ውስጥና ከቤት ውጭ መዝናኛዎችን ያካተተው ይህ ፕሮጀክት ባለ ሶስትና አምስት ኮከብ ሆቴሎችን የያዘ መሆኑም ተገልጿል።

የሁሉም ባንኮች አገልግሎት መስጫ ፣የተሽከርካሪዎች ነዳጅ ማድያ እና የጥገና አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎችም የሚገነባለት መሆኑን ከፕሮጀክቱ ማናጀር ኢንጂኒየር ብርሃነመስቀል አምባዬ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ፕሮጀክቱ በግንባታ ወቅትም ሆነ ከግንባታ በኋላ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ እድል እንደሚፈጥርም የፕሮጀክት ማናጀሩ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም