የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ ይጠናቀቃል
ግንቦት 3/ 2011 48ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ በሚደረጉ 13 ውድድሮች ፍጻሜውን ያገኛል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም እየተካሄደ የሚገኘው ውድድሩ አምስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን በዛሬው እለት 11 የፍጻሜና አራት የማጣሪያ ውድድሮች ተካሂደዋል።
ፍጻሜቸውን ካገኙት ስፖርቶች መካከል የሴቶች ሶስት ሺህ መሰናክል አንዱ ሲሆን አትሌት ብርቱካን አዳሙ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ 10 ደቂቃ ከሶስት ሰከንድ ከ3 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት አንደኛ በመሆን አጠናቃለች።
አትሌት መቅደስ አበባ ከአማራ ክልል አንድ ሰከንድ ከ37 ማይክሮ ሰከንድ በመዘግየት 10 ደቂቃ ከአራት ሰከንድ ከ40 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
አትሌት ወይንሸት አንሳ ከፌዴራል ማረሚያ 10 ደቂቃ ከስምንት ሰከንድ ከ68 ማይክሮ ሰከንድ ሶስተኛ በመሆን አጠናቃለች።
ከዚህ ውጭ ዛሬ ፍጻሜያቸውን ካገኙት ስፖርቶች መካከል የሴቶች ከፍታ ዝላይና ጦር ውርወራ ይገኙበታል።
በወንዶች ደግሞ 110 ሜትር የመሰናክል ሩጫና አሎሎ ውርወራ ፍጻሜቸውን ካገኙ የአትሌቲከስ ስፖርቶች መካከል ናቸው።
ለስድስት ተከታታይ ቀናት የሚደረገው ይህ ውድድር ነገ በሚደረጉ 13 ውድድሮች ፍጻሜውን የሚያገኝ ይሆናል።
በነገው የውድድሩ መዝጊያ እለት ከሚጠበቁት ውድድሮች መካከል በሁለቱም ጾታዎች የሚደረጉት የአምስት ሺህ እና የአንድ ሺህ 500 ሜትር የሩጫ ውድድሮች ይጠበቃሉ።
በተመሳሳይ በወንዶች ሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል ነገ ፍጻሜቸውን ከሚያገኙና በአትሌቲክስ ስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በአጓጊነትና ከሚጠበቁት ውድድሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ በነገው የውድድሩ ማጠናቀቂያ እለት የሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ስፖርት ተግባራትና፣የእርምጃ ውድድሮችና አጫጭር ርቀቶች መካከል ፍጻሜቸውን የሚያገኙ ስፖርቶች ይደረጋሉ።