ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የትራንስፖርት እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴሮችን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የትራንስፖርት እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴሮችን ጎበኙ
ግንቦት 3/ 2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የትራንስፖርት እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ጎበኙ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመስሪያ ቤቶቹ በመዘዋወር የተለያዩ የስራ ክፍሎችን የጎበኙ ሲሆን ቢሮዎችን የማስዋብና ለስራ ምቹ የማድረግ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች ላይ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን በአዲስ መልክ ማዋቀራቸውን ተከትሎ ሚኒስትሮች የ100 ቀናት ዝርዝር የሥራ እቅድ እንዲያዘጋጁ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በጉብኝቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለስራ ምቹ በማድረግ ረገድ ያከናወናቸውን ተግባራት ተመልክተዋል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ለስራ ምቹ የሆነ ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ አስፈላጊው እንቅስቃሴ እንደተደረገና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምቹ የስራ ሁኔታን ለመፍጠር ከሰራው ስራ በተጨማሪ ራሱን መልሶ በማደራጀት ሂደት ውስጥ ሰራተኞች አሉ የሚሏቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች አንስተው እነሱን የመፍታት ተግባር እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።
የሰራተኛ ካፍቴሪያና በአደረጃጀት ዙሪያ ከሰራተኞች የተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በለውጥ ማዕቀፍ ውስጥ በማካተት መፍትሄ ለመስጠት ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያደረጉት ጉብኝት እንዳስደሰታቸውና ጉብኝቱ የተጀመሩ ስራዎችን በተሻለ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ለመስራት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰሩ ስራዎች ለሌሎች የመንግስት ተቋማት ተሞክሮ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ዘመናዊና ምቹ የማድረግ ስራ ዶክተር አብይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በነበሩበት ወቅት የጀመሩት እንደሆነና በማሻሻያው ወቅት ይህንኑ የማስቀጠል ተግባር መከናወኑን ጠቅሰዋል።
የአንድ አገር መሪ በተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን የመመልከትና የመገምገም ልምድ ተቋማት የተሻለ የስራ ሁኔታ እንዲፈጥሩ ይበልጥ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በተቋማቱ ትርጉም ያለው ለውጥ ማየታቸውንና ይህንኑ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአምስት ወር በፊት የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን መጎበኘታቸው ይታወሳል።