በትግራይ ክልል ‘‘ሳልሳይ ወያነ ትግራይ‘‘ የተባለ አዲስ ፓርቲ ተቋቋመ

78

መቀሌግንቦት 2 / 2011 ለትግራይ ህዝብ አዳዲስ ሃሳቦችና አማራጮችን ይዤ መጥቻለሁ ያለው “ሳልሳዊ ወያኔ ትግራይ” ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

በቅርቡ የተመሰረተው የፓርቲው ጊዝያዊ አስተባባሪ ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ዓብለሎም ገብረሚካኤል ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ፓርቲው የፌዴራላዊ ስርዓት አወቃቀርን ተቀብሎ የሶሻል ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን የሚያራምድ ነው።

ፓርቲው ለትግራይ  ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም እንደሚሰራ ያስታወቁት አስተባባሪው “በህገ-መንግስቱ የሚገኙ የትግራይ ህዝብን ጥቅም የሚያስጠብቁ አንቀፆችን በመውሰድ የማይቀበላቸውን በውይይት እንዲሻሻሉ ይሰራል” ብለዋል።

“ሳልሳዊ ወያነ ትግራይ ለአዲሱ ትውልድ አዲስ ራእይና አዲስ ሃሳብ ለማስተናገድ የመጣ ፓርቲ ነው” ያሉት ደግሞ ሌላው የፓርቲው ጊዚያዊ አስተባባሪ አቶ ፀጋዘአብ ሺሻይ ናቸው።

“ፓርቲው በኢትዮጵያ የመደብ ጭቆና አለ ብሎ የተነሳ ፓርቲ ነው” ያሉት አቶ ፀጋዘአብ፣ ጠንካራና ዘላቂ በሰዎች ያልተንጠለጠሉ የስራና የዴሞክራሲ ተቋማት መገንባት ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ይሰራል።

ትኩረቱ እርሻ፣ ኢንዱስትሪ፣ቱሪዝምና ሌሎች የኢኮኖሚ ምንጮችን በእኩል የሚያራምድ ስርአት እንዲኖር ማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

የትግራይ ኢኮኖሚ የክልሉን እምቅ ሃብት መሰረት ያደረገና ማእከሉ ትግራይ የሆነ ኢኮኖሚ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ፓርቲ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የፓርቲው ጊዚያዊ አስተባባሪ አቶ ሃያሉ ጎደፋይ ናቸው።

ፓርቲው የሚመራበትን ፖሊሲና ስትራተጂ በቅርብ ጊዜ አዘጋጅቶ በጠቅላላ ጉባኤው አመራሩን ከመረጠ በኋላ ወደ ህዝብ ወርዶ እንደሚሰራ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም