ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገው ሽግግር ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ ሕዝቡ ሊታገስ ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገው ሽግግር ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ ሕዝቡ ሊታገስ ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
ግንቦት 2/2011 ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገው ሽግግር ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ ሕዝቡ ሊታገስ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስገነዘቡ።
ሕግ ማስከበር ላይ ያተኮረው አዲስ ወግ የምሁራን የምክክር መድረክ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ሲካሄድ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ቁርጠኛ አቋም መያዙንም ተናግረዋል ።
በምክክሩ ላይ ምሁራን መነሻ የሚሆን ሀሳብ አቅርበው ውይይት የተደረገ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ተሳታፊ በመሆን ነው ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
''ከዚህ በፊት ዴሞክራሲ ሲባል ሰማን እንጂ በተግባር አልታየም ፤ ዴሞክራሲን በተግባር ለማየት ልምምድ ይጠይቃል፤ ህዝቡ ለዚህ የሚሆን ጊዜ ሊኖረው ይገባል" ብለዋል።
በኢትዮጵያ ብዙ ፍላጎት ያላቸው አካላት ያሉ በመሆኑ ሁሉንም አነጋግሮ ወደ ስምምነት ለማምጣት ጊዜ እንደሚጠይቅ ገልጸው ዴሞክራሲ አካታች መሆንን ይጠይቃል የሚለውን መርህ ከግምት ማስገባት ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይ የሕግ የበላይነት ማስከበር ላይ መንግሥት ከመጠን በላይ እየታገሰ ነው የሚል ሀሳብ ሲሰነዘር ይደመጣል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ " መንግሥት ኃይል መጠቀም አቅቶት" እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
ከዚህ በፊት የነበሩ መንግስታት ኃይል ተጠቅመው ዜጎችን ሲቀጡ ነበር ግን ውጤት አልተገኘም ሲሉም ነው ያስረዱት።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ አገሪቱ ላይ ስጋቶች ቢታዩም በጽናት ማለፍ ከተቻለ ወደኋላ የማይመለስ ዴሞክራሲን መትከል ይቻላል።
በኢትዮጵያ ኃላፊነት ከመውሰድ ይልቅ አንዱ ሌላውን መውቀስ ላይ ትኩረት ተደርጓል በማለትም ወቀሳና ትችት በማቅረብ ብቻ ለውጥ አይመጣም ሲሉ ተናግረዋል።