የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እርምጃዎች ተወስደዋል - ኢዜአ አማርኛ
የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እርምጃዎች ተወስደዋል
ግንቦት 2/2011 የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ባለፉት ሁሉት ወራት ተቋማት የተለያዩ እርምጃዎች መውሰዳቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን ዛሬ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተለያዩ ተቋማት ባለፉት ሁለት ወራት የንግድና ኢንቨሰትመንት ዘርፉ ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት ስለተወሰዱ እርምጃዎች ለባለሃብቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም ገቢዎች ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የአዲስ አበባ መሬት ምዝገባና ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ ባለፉት ሁለት ወራት ንግድና ኢንቨስትመንት ላይ የወሰዷቸውን ማሻሻያዎች አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ያሉ የአሰራር ችግሮች ላይ ዝርዝር ጥናት ተደርጎ መፍትሄ እየተፈለገ ነው ብለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ፣ የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ፣ ንብረት አመዘጋገብ፣ የብድርና የሃይል አቅርቦት እንዲሁም የኪሳራ ሂደት ይገኙበታል።
የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዘላቂ ፈጣንና አስተማማኝ እንዲሆን የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን መፍታት ይገባል ብለዋል።
የብሄራዊ ባንክ ዋና ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እንዳሉት የአለም ባንክ በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሰረት ቢዝነስን በማሳለጥና ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ኢትዮጵያ ከ190 የአለም አገሮች 159ኛ ደረጃን አግኝታለች።
ይህን ደረጃ ለማሻሻልም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሙ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት ከተከናወኑ ስራዎች የብድር ስርዓቱን ማሻሻልና ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና በማስያዝ ብድር የሚሰጥበት ሁኔታ መመቻቸቱን አንስተዋል።
ቀደም ሲል በአገሪቱ የተደራጀ የብድር ተበዳሪዎች መረጃ አለመኖሩንና እስካሁን ድረስ ከ222 ሺህ የማይበልጡ የባንክ ተበዳሪዎች እንዳሉ የተናገሩት ዶክተር ይናገር ይህ በዓለም ባንክ መስፈርት መሰረት ዝቅተኛ ደረጃ የሚያሰጥ ነው ብለዋል።
የአንድ ተበዳሪ መረጃ በተደራጀና በተሟላ መልኩ መቀመጡ ለንግድና ኢንቨስትመንቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ከባንክ ተበዳሪዎች ውጭ አምሰት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዜጎች ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብድር ይወስዳሉ በሊዝ ካፒታል ደግሞ ሶስት ሺህ ተበዳሪዎች አሉ ነው ያሉት።
ይህ ተደምሮ በአገሪቷ ከስድስት ሚሊዮን የማይበልጥ የተበዳሪ መረጃ ያለ ቢሆንም ይህ መረጃ ተደራጅቶ በብሄራዊ ባንክ የመረጃ ቋት አልገባም ብለዋል።
በመሆኑም ባለፉት ሁለት ወራት ከሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ የተበዳሪዎች መረጃ ተደራጅቶ መግባቱን ዶክተር ይናገር አመልክተው ቀሪዎቹንም በቀጣይ ወራቶች ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው በኩላቸው ተቋማቸው ባለፉት ጥቂት ወራት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያከናወናቸውን ተግባራት አስረድተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ባለሃብቶችም በተቋማቱ እየታዩ ያሉ ማሻሻያዎች ዘላቂ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
አገራዊ የንግድ ከባቢ ሁኔታ ማሻሻያ ትግበራ መርሃ-ግብር በታህሳስ 2011 ዓ ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በይፋ መጀመሩ ይታወቃል።