መንግስት የህግ የበላይነትን ማስፈን አቅቶታልን? - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የህግ የበላይነትን ማስፈን አቅቶታልን?
ግንቦት 2 / 2011 መንግስት የህግ የበላይነትን ማስፈን አቅቶታልን? የሚለው ሃሳብ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዲስ ወግ በሚል ያዘጋጀው ውይይት ላይ ምሁራንን ሲያከራክር ውሏል።
በመድረኩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህን ዶክተር ዳኛቸው አሰፋና ዶክተር ጌታቸው አሰፋ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የተቀሙ ፕሬዝዳንት ና የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የመወያያ መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል።
ውይይቱ በዋናነት በዴሞክራሲያዊ ሽግግር ወቅት የህግ የበላይነት ላይ ያሉትን ፍልስፍናዊ፣ ሃሳባዊና ተቋማዊ መሰረቶችን መመርመርን ያለመ ሲሆን፤ መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር አቅቶታልን የሚለው ሃሳብ ላይ ከፍተኛ ሙግት ተደርጓል።
የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በዚህን ወቅት ስልጣንና ኃይል ከተነጣጠሉ የህግ የበላይነትን ማሰብ የዋህነት መሆኑን አስረድተው፤ የዶክተር አብይ መንግስት ይህን ከማድረግ ይልቅ ፖለቲካዊ ማባባል ላይ አተኩሯል ብለዋል።
"ጠቅላይ ሚንስትሩን ሳስባቸው አንድ እግራቸው ወደ ዴሞክራሲና ነጻነት ተሻግሮ ሌላኛው እግራቸው ደግሞ እንዳይንቀሳቀስ ሆኖ በብሄር ጽንፈኞች ተተብትቦ ይታዩኛል" ሲሉም ገልጸዋል።
የህዝብ አመጽና አብዮት በበደል ብቻ ሳይሆን በመንግስት ደካማነት ምክንያት ሊፈጠር እንደሚችል በመጠቆም።
ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው የጸጥታ አካላትን ጨምሮ እንደ አገር የነበርንበት ሁኔታ በተዛባ መሰረት ላይ ስለነበረ አሁን የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል ጊዜ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
መንግስት እነዚህን ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት ነጻ በር መክፈቱን አስታውሰው፤ ይህ እርምጃ እንደማባበል ሊወሰድ አይገባም ነው ያሉት።
በህግ የተቀመጡ መብቶችና ከህግ አግባብ ይልቅ በራስ ጉልበት ለማሻሻል መሞከር ግዴለሽነትን ማስከተሉ ስለማይቀር ጥንቃቄ አንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ ዶክተር ጌታቸው አሰፋ ናቸው።
ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የህግ የበላይነትን ያለ ጠንካራ የህግ አስከባሪ ተቋማት ማሰብ እንደማይቻል ጠቁመው፤ መንግስት ይህን እውን በሚያደርግ ተቋማዊ ለውጥ ወስጥ እንደሚገኝ አውስተዋል።
ማህበረሰቡም የፍትህ መስፈን ጥቅሙ ለራሱ መሆኑን ተረድቶ በሚጠበቅበት ልክ ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ድንገት ከተሳታፊዎች መካከል የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በስም እንጂ በተግባር አናውቀውም ሲሉ ተናግረዋል።
ዴሞክራሲያዊ ልምምድን ለማስፈን ጊዜ እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል። ይህ ማለት ግን መንግስት ኃይል የለውም ማለት አለመሆኑን ገልጸዋል።
"እጁ ላይ ኃይል ያለው አካል ሁሌም ታጋሽ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚነስትሩ፤ የመንግስትን ትዕግስት መፈታተን ግን ብዙ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል አሳስበዋል።
መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስፈን በሚችልበት ሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።