የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ የወቅቱ የኢትዮጵያ አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄ መሆኑን ጥናት አመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ የወቅቱ የኢትዮጵያ አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄ መሆኑን ጥናት አመለከተ
ግንቦት 2/2011 በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ የወቅቱ አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄ መሆኑን በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የተካሄደ የህዝብ አስተያየት ጥናት አመለከተ።
የአንድ ዓመቱን የለውጥ ጉዞ በማስመልከት ለመገናኛ ብዙሃን አጀንዳና ለመንግስት አካላት ግብረመልስ እንዲሆን በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተካሄደው ፈጣን የህዝብ አስተያየት ጥናት እንዳመለከተው የህግ የበላይነትን የማስፈን ጉዳይ የህዝቡ ቀዳሚ ጥያቄ ነው።
ከመጋቢት አጋማሽ አንስቶ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በተካሄደው በዚሁ ጥናት ከኦሮሚያ ነቀምት፣ ጎባ፣ ነገሌ ቦረና፣ ፍቼ፣ አዳማ፣ ጭሮና ጅማ፣ ከአማራ ባህርዳር፣ ደሴ፣ ጎንደርና ደብረማርቆስ፣ ከትግራይ መቀሌና ሽሬ፣ ከደቡብ ህዝቦች ሐዋሳ፣ ወላይታ ሶዶና ሆሳዕና እንዲሁም ሐረር፣ ድረዳዋ፣ ጅግጅጋ፣ ሰመራ፣ ጋምቤላና አሶሳ ከተሞች ተካተዋል።
በእነዚህ ከተሞች ከሚኖሩት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አንድ ሺ ሰዎች በጥናቱ የተሳተፉ ሲሆን፤ የህግ የበላይነትን የማስፈን ጉዳይ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ 76 ነጥብ 2 በመቶዎቹ በምላሻቸው ጉዳዩ አንገብጋቢና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን አመልክተዋል።
የህግ የበላይነትን ከማስከበር ጋር በተያያዘ ከጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል 59 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆኑት የጸጥታ ችግር ሲያጋጥም 'መንግስት ፈጣን ምላሽ እየሰጠ አይደለም' የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በተመሳሳይ 54 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች የህግ አስከባሪዎች ሚናቸውን በተገቢው እየተወጡ አይደሉም ሲሉ መልሰዋል።
በመላሾቹ ለአብነት ከተነሱት ጉዳዮች መካከልም የዜጎች ሞትና መፈናቀል መበራከት፣ ለህግ የማይገዙ የሚመስሉ አክቲቭስቶች እንቅስቃሴ በዝምታ መታለፍ፣ የመንጋ ፍርድ፣ መብትን መጠየቅ እንጂ ግዴታን አለመወጣትና በአንፃሩ የመንግስት ከልክ ያለፈ ሆደ ሰፊነት መኖር ተጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የተለያዩ ተዋናይ አካላት ሚና ላይ የህዝቡን አስተያየት ለማወቅ በቀረበላቸው ጥያቄ ከጥናቱ ተሳታፊዎች 46 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የህዝቡን አብሮነት እሴቶች ከማጎልበት በተቃራኒ ይሰራሉ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
እንዲሁም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎች ማለትም 54 ነጥብ 4 በመቶዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና አክቲቪስቶች አገራዊ አንድነትን ከማጠናከር አኳያ ሚናቸውን በአግባቡ እየተወጡ አለመሆኑን በምላሻቸው አመልክተዋል።
ከለውጡ ጋር በተያያዘ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ለጥናቱ ተሳታፊዎች በቀረበው ጥያቄ በየደረጃው በሚገኘው የመንግስት መዋቅር ህብረተሰቡ ተገቢ አገልግሎት እያገኘ አይደለም የሚል ምላሽ የሰጡት የጥናቱ ተሳታፊዎች 48 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ ይዘዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የግልጽነትና ተጠያቂነት ስርዓት እየተሻሻለ አለመሆኑን የገለጹት 41 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑት መላሾች ናቸው።
በአንድ ዓመቱ የለውጥ ጉዞ የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ አብዛኛዎቹ የጥናቱ ተሳታፊዎች ማለትም 62 በመቶዎቹ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በተወሰዱ ማሻሻያዎች የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቷል ብለው የሚያምኑ መሆኑን የጥናቱ ግኝት አሳይቷል።
ሆኖም ግን 41 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት መላሾች እየተካሄደ ያለው አገራዊ ሪፎርም ግልጽ የፖለቲካ አቅጣጫ ላይ ተመስርቶ እየተጓዘ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልፀዋል።
ከጥናቱ ተሳታፊዎች ግማሽ ያህሉ ለውጡን ተከትሎ ሰላምና አብሮነትን ለማጎልበት የተካሄዱ የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች ለውጥ አምጥተዋል ብለው የሚያምኑ መሆኑን በምላሻቸው ገልጸዋል።
በዲፕሎማሲ ግንኙነቶችና በኢኮኖሚው መስክ በተካሄዱ የሪፎርም እርምጃዎች ዙሪያ አብዛኛው የጥናቱ ተሳታፊዎች አዎንታዊ ምልከታ ያላቸው መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከዜና ዜና ነክ መረጀ አቅርቦት በተጨማሪ ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮችን እየመረጠ የህዝብ አስተያየት በማጥናት ግኝቱ ለመገናኛ ብዙሃን አጀንዳ፣ ለመንግስትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ደግሞ ግብረ መልስ እንዲውል እያደረገ ይገኛል።