በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየውን አለመግባባት በዘላቂነት እንዲፈታ ኢህአዴግ ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየውን አለመግባባት በዘላቂነት እንዲፈታ ኢህአዴግ ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲረግብና ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲመለስ ኢህአዴግ ጥሪ አቀረበ። የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ዛሬ ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ አስመልክቶ በላከው መግለጫ በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ለዓመታት ተፈጥሮ የቆየውን አለመግባባት በማርገብ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቧል። "ሰላም ከሁሉም በላይ ነው፤ ሰላም ሲኖር የአገርን እድገትና የሕዝቦችን በሰላም ወጥቶ የመግባት እንቅስቃሴ ዋስትና መስጠት ይቻላል" ያለው መግለጫው፤ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረው ደም አፋሳሽ ጦርነት የብዙ ሕዝቦችን ሰላም ማቃወሱን አስታውሷል። በአገሮቹ መካከል በተደረገው ጦርነት በሁለቱም በኩል ቤተሰቦች ተበትነዋል፣ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች "ሁሌም ያለመረጋጋትና የስጋት ስነ-ልቦና ሰለባ ሆነው ቆይተዋል" በሚልም ገልጾታል። በሁለቱም አገሮች ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ መፈጠሩን መግለጫው አመልክቶ፤ በድንበር አካባቢ በንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች ላይ ተፅእኖ መፈጠሩንም ነው ያብራራው። ይህ በመሆኑም "የሁለቱ አገሮች የወደፊት ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል?" የሚለው ጥያቄ የአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት መደረጉን አስታውሶ፤ ላለፉት 20 ዓመታት በአገሮቹ መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ዝምታ ተፈጥሮ መቆየቱን አውስቷል። በአሁኑ ወቅት በአገሮች መካከል የእውነት ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው የተለየ አቋምና አካሄድ እንደሚያስፈልግ ያመለከተው መግለጫው፤ ሁለቱም መንግሥታት "ለህዝባቸው ምርጫና ፍላጎት ቦታ የሚሰጡ ሊሆኑ ይገባል" ሲልም አትቷል። "እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ የሚል ፉክክር ለሁለቱም ህዝቦች የሚፈይደው ነገር አይኖርም" ያለው መግለጫው፤ ለአፍሪካ ቀንድ አገሮችና አካባቢያዊ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት ዘላቂው መፍትሔ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጤናማ ግንኙነት መመሥረት መሁኑንም ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱም ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን በመግለጫው ገልጿል። የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሰላም ጥሪውን እንዲቀበል የጠየቀው ኮሚቴው፤ በሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች አብሮነትና ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ ጥሪውን አቅርቧል።