የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መከታተላችን ተጠቃሚ አድርጎናል- የቦዲቲ አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መከታተላችን ተጠቃሚ አድርጎናል- የቦዲቲ አርሶ አደሮች
ሶዶ ግንቦት 2/2011 የተቀናጀ የተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መርሃ ግብር በመከታተላቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን በወላይታ ዞን የቦዲቲ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
የአርሶ አደሮችን ተሳትፎ ለማሳደግ ተሞክሮ በመቀመር፣ ማዕከላትን በሰው ሃብትና በግብዓቶች በማሟላት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም የዞኑ ትምህርት መምሪያ ገልጿል፡፡
አርሶ አደር አባይነህ በርገነ በአስተዳደሩ የጮጫ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፣ ከ2004 ጀምሮ በተሰጣቸዉ ስልጠና መሠረት በራሳቸው ተነሳሽነት ማዕከል በመክፈት ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ምሳሌ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
ትምህርቱ ለማሳቸው የሚያስፈልጉ የግብዓቶችን መጠን፣ ልኬትንና ጊዜን በመረዳት ከብክነት መዳናቸውንና ምርታቸውን ማሳደጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
በትምህርቱ በጣት ከመፈረም መውጣታቸውንና ልጆቻቸው ከትምህርት መልስ የተማሩትን መከታተልና መቆጣጠር እንዳስቻላቸውም የፎኦ አካባቢው ነዋሪ አርሶ አደር አልማዝ ሴታ አመልክተዋል።
ትምህርቱን ከጀመሩ ሁለተኛ ዓመት መያዛቸውንና በተለይም በሚሰጣቸው የጤና ትምህርት የራሳቸውን፣የቤታቸውንና የአካባቢያቸውን ንጽህና የመጠበቅ በሽታን ለመከላከል እንዲሁም ወጪና ጊዜን ለመቆጠብ ችያለሁ ይላሉ።
የቦዲቲ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በለጠ ዳካ የጎልማሶች ትምህርት መሰጠቱ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እንዳደረገው ይናገራሉ።
በአስተዳደሩ ዘጠኝ ቀበሌዎች በተከፈቱት ከ27 በላይ የመማማሪያ ማዕከላት ከ1 ሺህ 700 በላይ ጎልማሶች ትምህርቱን እየተከታተሉ ናቸው ብለዋል።
ትምህርቱ በግብርና፣በጤናና ቁጠባን አካትቶ እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
ትምህርቱን ከህዝብ ፍላጎትና ተጠቃሚነት አንጻር ተደራሽና ውጤታማ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንዲፈጥሩ አቶ በለጠ ጠይቀዋል፡፡
በወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ጎልማሶችና መደበኛ ያልሆኑ ትምህርት ዳይሬክተር አቶ አማን ሳታ እንደገለጹት በዞኑ በሚገኙ በሁሉም መዋቅሮች የትምህርት ዝግጅት፣ልምድና ፍላጎትን ታሳቢ ያደረገ የሰው ኃይል መሟላቱ በአፈጻጸም ላይ መሻሻል እንደታየበት ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ከ1ሺህ130 በላይ አመቻቾችንና ባለሙያዎች መመደባቸውን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ከ150 ሺህ ብር በላይ ወጪ በብሄሩ ቋንቋ መጽሐፍ ታትሞ ጥቅም ላይ መዋሉን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
በዞኑ 150ሺህ የሚደርሱ ጎልማሶች በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን በ2ሺህ በላይ የመማሪያ ጣቢያዎች እየተከታተሉ ነው፡፡