የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚያስችል ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል ተባለ

ግንቦት 1/2011 በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት የንባብ ባህልን ለማዳበርና ለማበረታታት የሚያስችል ስርዓት መፍጠር እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ ለተቋሙ ሰራተኖች ያዘጋጀው ሳምንታዊ የንባብ ጊዜ መርሃ ግብር ዛሬ ይፋ ተደርጓል። 

በየሳምንቱ በእለተ ረቡእ ለአንድ ሰዓት የሚካሄደው የሰራተኞቹ የንባብ ጊዜ መርሃ ግብር ይፋ በተደረገበት ስነ-ስርዓት ላይ በሚኒስቴሩ አማካሪና ተወካይ የሆኑት አቶ ወርቅነህ አክሊሉ እንደገለጹት፤ ማንበብን መሰረት በማድረግ ትውልድ ቀረጻ ላይ የሚከናወነው ተግባር አነስተኛ ነው። 

እንደ አቶ ወርቅነህ ገለጻ ማንበብ ሰዎች አካባቢያቸውን ብሎም ዓለምን የሚያዩበት፣ ህይወታቸውን የሚመሩበትን መንገድ የተዋጣለት ለማድረግ የሚያግዝ እውቀትን ያጎናፅፋል።

በተለይ ትምህርት ቤቶች ና ሌሎች የእውቀት ማዕከላት ደግሞ ይህንን ዓይነት ባህል ለማዳበር የሚያስችሉ መሰረቶች በመሆናቸው ወጣቶች የንባብ ባህልን እንዲያዳብር ማበረታታት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ይህም በዕውቅት ላይ የተገነባ ትውልድ ከመፍጠር ባሻገር  በራሱ የሚተማመንና አገርን የሚጠቅም ዜጋ ለመጠፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ የዚህ ዓይነቱን ባህል ማዳበር እንዲቻል ተቋማት በሳምንት አንድ ቀን  ለሰራተኞቻቸው የማንበቢያ ጊዜ በመስጠት የንባብ ልምድን ማበረታታት ይችላሉ ሲሉም ገልፀዋል።

ወላጆች ልጆችን ሲያሳድጉ በፊልሞችና መሰል ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ከማበረታታት ይልቅ ከተረት መፅሀፍ ጀምሮ በየደረጃው የተዘጋጁ ጠቃሚ መጻፍትን  በማቅረብ የንባብ ልምድ እንዲያዳብሩ የማነፅ ኃላፊነት እለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም