አገር አቀፍ የጠረጴዛ ቴኒስ የክለቦች ሻምፒዮና የፊታችን ሰኞ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀፍ የጠረጴዛ ቴኒስ የክለቦች ሻምፒዮና የፊታችን ሰኞ ይጀምራል
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2011 ሁለተኛ ዙር የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ሻምፒዮና ከግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል።
በሻምፒዮናው ላይ በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ኤሌትሪክ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ፣ ማማስ ኪችን፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ እና የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) ይሳተፋሉ።
በሁለቱም ጾታዎች በነጠላ፣ በጥንድ( ወንድ እና ወንድ )፣ በድብልቅ (ወንድና ሴት) እና የቡድን የዙር ውድድር ሻምፒዮና የሚካሄድባቸው ዘርፎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አበባ አማረ ለኢዜአ እንደገለጹት የሻምፒዮናው ዓላማ ከነሐሴ 13 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ ከተማ ራባት በሚካሄደው 12ኛው የአፍሪካ የመላ ጨዋታ ውድድር የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ ነው።
በተጨማሪም ለክለቦች የውድድር አማራጮችን ማስፋትና ብቃት ያላቸውን የጠረጴዛ ቴኒስ ተወዳዳሪዎች ለመመልመልም ሻምፒዮናው ወሳኝ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በሻምፒዮናው የሚያሸንፈው ክለብ ከሐምሌ 24 እስከ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በናይጄሪያ ሌጎስ ከተማ በሚካሄደው 25ኛው የአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክሎ እንደሚሳተፍም ጠቁመዋል።
በጥር ወር 2011 ዓ.ም በጅማ ከተማ በተካሄደው የ2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ አሸናፊ ነበር።
በዘንድሮው ዓመት ከክለቦች ውድድር በተጨማሪ የግል የበላይነት፣ የታዳጊዎች፣ የሴቶችና የተማሪዎች ውድድሮች እንደተካሄዱ የገለጹት ኃላፊዋ የዘንድሮው ውድድር ከባለፉት ዓመታት የውድድር አማራጮች የሰፉበት እንደሆነም ተናግረዋል።
የ2011 ዓ.ም ሁለተኛ ዙር የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ሻምፒዮና እስከ ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ውሃ ዋና የክልሎችና የክለቦች ሻምፒዮና ከግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በቢሾፍቱ መኮንኖች ክበብ ይካሄዳል።
በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች እንዲሁም የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ እና ቢሾፍቱ የውሃ ዋና ስፖርት ክለቦች ይሳተፋሉ።
ነጻ ቀዘፋ፣ የጀርባ ቀዘፋ፣ ደረት ቀዘፋ እና ቢራቢሮ እንዲሁም ድብልቅ ወይም ነጻ ቀዘፋ፣ የጀርባ ቀዘፋ፣ ደረት ቀዘፋ እና ቢራቢሮን በማጣመር ውድድር የሚካሄድባቸው ዘርፎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቀልቤሳ ኤባ ለኢዜአ እንደገለጹት ሻምፒዮናው የሚካሄደው የተለያዩ ዓላማዎችን ታሳቢ በማድረግ ነው።
ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እርስ በእርሳቸው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ፣ የክለቦችን ተሳትፎ መጨመርና ክለቦችን ማጠናከር፣ በ2011 ዓ.ም መጨረሻ እና በ2012 ዓ.ም በሚካሄዱ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመመልመልና ለመመምረጥ እንዲሁም ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሆነም ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የክለቦች እና የክልሎች ውድድር በተናጠል ሲካሄዱ እንደነበረ ያስታወሱት ኃላፊው ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱንም በማጣመር ጠንካራ ውድድር ለማካሄድ መታቀዱን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ውሃ ዋና የክልሎችና ክለቦች ሻምፒዮና እስከ ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።