ኢትዮጵያ በፈረንሳይ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ልትሳተፍ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በፈረንሳይ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ልትሳተፍ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2011 ኢትዮጵያ በዘንድሮው የካን አለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ልትሳተፍ መሆኑን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አስታወቀ።
የ2019ኙ የካን አለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከግንቦት 14 እስከ 25 ድረስ በፈረንሳይ ካን ከተማ ይካሄዳል።
የካን አለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ፤ ከረዥም አመታት በፊት ሲቋቋም ለሲኒማ ጥበብ እድገት አስተዋፅዖ ያደረጉ ባለሙያዎችንና ሥራዎቻቸውን በማስተዋወቅ ሲኒማን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማክበር አላማውን አድርጎ ነው።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን ይህንን አስመልክተው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኢትዮጵያ በካን አለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ትሳተፋለች።
ፊስቲቫሉ ኢትዮጵያን በአለም አቀፍ መድረክ ላይ ከማስተዋወቅ ባሻገር ለቱሪዝም ሴክተሩ ከፍ ያለ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ለአገር ገጽታ ግንባታ ብሎም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ስለ አለም አቀፉ የፊልም ኢንዱስትሪ ሁኔታና ገበያ የሚያጠና ቡድን የፊልም ፌስቲቫሉ ወደ ሚካሄድበት ፈረንሳይ ካን ከተማ እንደሚያቀና ተናግረዋል።
የልኡካን ቡድኑ ከአለም አቀፍ የፊልም ኢንደስትሪ ገበያ በተጨማሪ ሌሎች የፈጠራ ኢንደስትሪዎችንም የሚያስሱ ይሆናሉ ብለዋል።
በፊልም ፌስቲቫሉ ላይ ለመታደምም በኢትዮጵያ የፊልም ሙያ የተሰማሩ ባለሙያዊችም ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ እንዲያድግ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ይህ አጋጣሚ መፈጠሩም ጥሩ እድል መሆኑን ተናግረዋል።
የአገሪቷን የፊልም ኢንደስትሪ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግም መንግስት ከግል ሴክተሩ ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የካን አለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን ዘንድሮ ሲከበር ለ72ኛ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።