ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይካሄዳሉ

ግንቦት 1/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳሉ። 

በሽሬ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ስሑል ሽረ ኢትዮጵያ ቡና የሚያስተናግድበት መርሃ ግብር የዚህ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ነው።

ከነገ በስቲያ በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ በፕሪሚየር ሊጉ ግርጌ ከተቀመጠው ደደቢት ጋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

እሁድ ግንቦት 4 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደቡብ ፖሊስ ይጫወታል።

በክልል ከተሞች እሁድ አምስት ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን በሀዋሳ ስታዲዮም በፕሪሚየር ሊጉ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሲዳማ ቡና የሊጉን መሪ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት የሚያስተናግድበት መርሃ ግብር የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነው።

በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ባህርዳር ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ፣ በአፄ ፋሲለደስ ስታዲዮም ፋሲል ከነማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ በጅማ ስታዲዮም ጅማ አባ ጅፋር ከሀዋሳ ከተማ እና በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲዮም አዳማ ከተማ ከመከላከያ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ48 ነጥብ ሲመራ፣ ፋሲል ከነማ በ43 ሲዳማ ቡና በ40 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል በ14 ግቦች ሲመራ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ13 የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በ11 ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም