ቀጥታ፡

ለግልገል በለስ ከተማ የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ 85 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ስምምነት ተፈረመ

አሶሳ ሚዝያ  30/2011በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለማስገንባት 85 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ስምምነት ዛሬ ተፈረመ፡፡

ስምምነቱን ዛሬ በአሶሳ ከተማ የተፈራረሙት የክልሉ ውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮና ሾዴብ ኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን የተባለ ድርጅት ናቸው፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አጠይብ መሐመድ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣውን የከተማዋን ህዝብ የውሃ ፍላጎት ጥያቄ ለመመለስ ያስችላል፡፡

ለፕሮጀክቱ  ማስፈጸሚያ ከሠላም ሚኒስቴር በተመደበው በጀት ሶስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ 19 አዳዲስና ነባር ቦኖዎችን ግንባታና እድሳት እንደሚከናወኑ አስረድተዋል፡፡

በሰከንድ ከ22 ሊትር በላይ ውሃ ማመንጨት አቅም የሚኖረውን ፕሮጀክት በአንድ ዓመት ውስጥ ለአገልግሎት ለማብቃት መታቀዱንም አቶ አጠይብ አመልከተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለቀጣይ 15 ዓመታት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

ሥራው በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ውይይት እንደሚደረግ የተናገሩት ምክትል ኃላፊው፣ የከተማው አስተዳደር ከይዞታ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከወዲሁ እንዲፈታ አሳስበዋል፡፡

የሾዴብ ኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተድላ ጫንያለው ነበበኩላቸው ፕሮጀክቱን በወቅቱ አጠናቀው ለማስረከብ ቃል ገብተዋል፡፡

ግልገል በለስ በ1994 የተቋቋመች የመተከል ዞን ዋና ከተማ ነች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም