ዔሊ በሚሊዮን ትሸጣለች በሚል የሚናፈሰው ወሬ ሀሰት ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ዔሊ በሚሊዮን ትሸጣለች በሚል የሚናፈሰው ወሬ ሀሰት ነው ተባለ
አዲስ አበባ ሚዝያ 30/2011የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን ዔሊ በሚሊዮን ትሸጣለች በሚል የሚናፈሰው ወሬ ሀሰተኛ ነው አለ።
ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት መሰረተ ቢስ ወሬዎች ራሱን እንዲጠብቅም አሳስቧል፡፡
ሰሞኑን "የውጭ ሽፋኗ ( ድንጋይዋ) እንደ ማግኔት ብረት የሚይዝ ፣ ኔትወርክ የምታጠፋ፣ ፎቶግራፍ የማትነሳ በፕላስቲክ ጠርሙስ ከአጠገቧ የተቀመጠ የውሃ መልክ የምትቀይር፣ ማታ ማታ እግሯ አካባቢ የምታበራ ዔሊ በሚሊዮን ትሸጣለች" የሚል ወሬ ሲንሸራሸር ሰንብቷል፡፡
በዚህ ወሬ ምክንያት ብዙዎች እየተጭበረበሩ ነው፤ ዔሊዎችም በህገ ወጥ መንገድ ታድነው ወደ ከተማ እየገቡ ለመኪና አደጋ ከመገላጣቸውም በላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እያሳለፉ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸዉ የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን የዱር እንስሳት እና ውጤቶቻቸው ዝውውር እና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጳዉሎስ ወሬው መሰረተ ቢስ እና ከዔሊ ሳይንሳዊ ባህሪ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ነው ይላሉ፡፡
አቶ ዳንኤል ጉዳዩ ከአሁን በፊት ሞዓ አንበሳ ባንዲራ ያለበት ትሪ፣ የድሮ ካውያ፣ ማሾ እና ፋኖስ እንገዛለን በሚል ከተሰራጨው መረጃ ጋር ተመሳሳይነት አለው የሚል እምነት አላቸው፡፡
መጀመሪያ መረጃው ከወደ ካርቱም እንደመጣ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ ሰሙኑን የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስታት የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለሙያዎች ውይይት ላይ ከሱዳን በኩል ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌለ ተረጋግጧል ነው ያሉት፡፡
ወሬው መሰራጨት ከጀመረ በትንሹ ሁለት ወር እንደሚሆነውና በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን፣ በአፋር ሚሌ እና በጎንደር መተማ አካባቢ በስፋት እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ በሁለት ወር ውስጥ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ሁለት ዔሊዎች ደግሞ በህገ-ወጥ መንገድ በሰዎች ሲዘዋወሩ ተይዘው ሆለታ እንስሳት ማገገሚያ ማዕከል ገብተዋል፡፡
የዱር እንስሳትን በህገ-ወጥ መንገድ መያዝ በመኖሪያ ቤት አካባቢ ማኖር፣ ማዘዋወር እና መሸጥ በህግ የተከለከለ ሲሆን እስከ አምስት ዓመት እስራት እና እስከ 30 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ በዱር እንሰሳት ልማት እና ጥበቃ አዋጅ 541/1999 ተደንግጓል፡፡
ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት መሰረተ ቢስ የሀሰት ወሬ ራሱን ከመጠበቅ ባሻገር እንስሳትን ከአላስፈላጊ እንግልት የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አቶ ዳንኤል አሳስበዋል፡፡