የኢጋድ የሚኒሰትሮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢጋድ የሚኒሰትሮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ
ሚያዝያ 30/2011 በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የተካሄደው 67ኛው የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ተጠናቅቋል።
የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የወቅቱ የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤትሰብሳቢ አቶ ገዱ አንዳርጋችው የስብሰባውን ውጤት በተመለከተ ለደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ገለጻ አድርገዋል።
አቶ ገዱ በገለጻቸው የደቡብ ሱዳን ተደራዳሪ ወገኖች ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት የቅድመ ሽግግር ጊዜው ለተጨማሪ 6 ወራት እንዲራዘም የደረሱበትን ስምምነት የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሙሉ በሙሉ መቀበሉንገልጸዋል።
በተደራዳሪ ወገኖች በኩል የተደረሱ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ 100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በመንግስት በኩል መመደቡን ምክር ቤቱ በአድናቆት እንደተመለከተውም ተናግረዋል።
ይህም ዓለም አቀፍ አካላት ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያነሳሳቸውም ሚኒስትሩ በገለጻቸው አብራርተዋል።
በተደራዳሪ ወገኖች የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ኢጋድ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ባደረጉት ገለጻ አረጋግጠዋል።