የብፁዕ አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ። - ኢዜአ አማርኛ
የብፁዕ አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ።
ሚያዝያ 30/ 2011 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊና በቤተክርስቲያኒቱ ለረጅም ዓመታት በከፍተኛ ኃላፊነት ያገለገሉት ብፁዕ አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈፀመ።
በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን በተፈፀመው የአቡነ ገሪማ ሥርዓተ ቀብር ላይ የቤተክርስቲያኗ ፓትርሪያርክ አቡነ ማቲያስ፣ አቡነ-መርቆርዮስ እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የአገሪቱ አብያተ ክርስቲያናት ሀገረ- ስብከት መሪዎች ተገኝተዋል።
የቀብር ስርዓቱ የተፈፀመው በፓትሪያርኩ አቡነ ማቲያስ መሪነት በተከናወነ ስርዓተ ፀሎት ነው።
የ74 ዓመቱ አቡነ ገሪማ በቤተክርስቲያኗ ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ፤ በእምነቱ ሊቅነታቸው በስፋት የሚታወቁ ታላቅ ኢትዮጵያዊ እንደነበሩ በስርዓተ ቀብሩ ላይ ተገልጿል።
በህይወት ዘመናቸውም በተለይ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምክትል አስተዳዳሪና ዋና ጸሐፊ፣ የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ ኃላፊ፣ በብሥራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ ደግሞ መምህር ሆነው አገልግለዋል።
አቡነ ገሪማ በሊቀ ጳጳስ ደረጃ የመጀመሪያው የጠቅላይ ቤተ-ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ እስኪያጅም ነበሩ።
እስካለፈው ሚያዝያ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስም በፓትርያርኩ ልዩ ጽህፈት ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊነት ሥራቸውን በማከናወን ላይ ነበሩ።
አቡነ ገሪማ በቤተ-ክርስቲያን ታሪክ የሥነ ጽሑፍ ስራና አስተምሮታቸው፣ በዓበይት በዓላት በሚያቀርቧቸው ታሪካዊና ሐዋርያዊ ተልዕኳቸው እንዲሁም በስብከት ጽሁፎቻቸውም በስፋት ይታወቃሉ።
እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ ከ30 በላይ ትምህርታዊ የስነ ፅሑፍ ስብስብና “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ” የሚል መጽሐፍ ለአንባብያን አድርሰዋል፡፡
በ1937 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ የተወለዱት ብፁእነታቸው በመንፈሳዊ ትምህርት ዜማን፣ ቅኔን እንዲሁም አቋቋምን ከተለያዩ መምህራንና የአብነት ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረር የራስ መኮንን አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡
እንዲሁም በንጉሱ ዘመን በ1958 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሮማንያ ተልከው በታሪክ ትምህርት የማስተርስ እና በነገረ-መለኮት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡
ማዕረገ ዲቁናቸውን ደግሞ ከግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ፤ ማዕርገ ምንኩስናን እንዲሁም ከደብረ ሊባኖስ ገዳም በ1973 ዓ.ም እንደተቀበሉ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡