በኢትዮጵያ ያለው የስፖርተኞች ምልመላና ስልጠና ምዘና ሂደቶች ብክነት እያስከተለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ያለው የስፖርተኞች ምልመላና ስልጠና ምዘና ሂደቶች ብክነት እያስከተለ ነው
ሚያዝያ 30/2011 በስፖርተኞች ምልመላ ስልጠና እና ምዘና ሂደቶች ላይ በባለድርሻ አካላት መካከል ያለው የተበጣጠሰ ቅብብሎሽ በስፖርቱ ዘርፍ ብክነት እያስከተለ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ትናንት በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሰልጣኞች ማህበር ሊቀመንበር ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ስፖርተኞችን የመመልመል የማሰልጠንና የመመዘን ተግባር እንደሚያከናውን ተናግረዋል።
ያም ቢሆን አካዳሚው የሚሰራውን ስራ በተመሳሳይ ብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦችና የስፖርት ድርጅቶችም እያከናወኑ በመሆናቸው የምልመላ ስልጠናና ምዘና ስርአቱ በተበጣጣሰ መልኩ እንዲካሄድ እያደረገ ነው ብለዋል።
አንድ ተመሳሳይ ተግባርን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየሰሩት በመሆናቸው የስራ ድግግሞሽ በመፍጠር የሰው ሃይልና የሀብት ብክነት እያስከተለ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ስራ ለመስራት የምልምላ ስልጠናና ምዘና ስርአቱ በተቀናጀ መልኩ መሰራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
የስፖርት ኮሚሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰለሞን አልዩ በበኩላቸው ከምልምላ እስከ ምዘና ባለው ሂደት ውስጥ በአካዳሚውና በሌሎች ባለድርሻ አካላት መካከል ያለው የቅብብሎሽ ሂደት ደካማ እንደሆነ አልሸሸጉም።
በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት መካከል የቅንጅት አሰራር ስርአት አለመዘርጋቱ የቅብብሎሽ ሂደቱን ውጤታማ እንዳይሆን እንዳደረገውም ጠቅሰዋል።
የስፖርቱን ልማት በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ ከተፈለገም በስልጠናው፣ በምልመላና ምዘና ላይ የስራ ክፍፍል ማድረግ የሚያስችል አካዳሚውና ባለድርሻ አካላት የጋራ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ወደ ተግባር መቀየር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ይህም እውን ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስፖርቱ ልማት ላይ ተጫባጭ ለውጥ ማየት እንደሚቻልም አመልክተዋል።
የስፖርት መሰረተ ልማቶች ላይ ለረጅም ዓመታት የግንባታ ተቆጣጣሪ ሆነው የሰሩት አቶ ጥበቡ ጎርፉ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ በሚሰራው ስራ ብቻ በስፖርቱ ልማት ላይ ለውጥ ማምጣት እንደማይችል ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች የስፖርት አካዳሚዎችን መገንባት እንደሚገባቸውና አካዳሚው በስፖርቱ ልማት ዘርፍ ያለውን ተሞክሮ ለክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ማካፈል እንደሚገባውም ገልጸዋል።
የቅንጅት አሰራሩን በተመለከተም አካዳሚውና ባለድርሻ አካላት ስራን በግልጽ የለየ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት እንደሚገባቸውም ጠቅሰዋል።
አካዳሚው የሚያደርጋቸውም ጥናትና ምርምሮችም መሰረታዊ የሆኑ የስፖርት ልማት ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው አካዳሚው ከባለድርሻ አካላት ጋር በምልምላ ስልጠናና ምዘና ላይ ለመስራት ዝግጁ እንደሆነና የተነሱትን ምክረ ሀሳቦች ተቀብሎ ወደ ተግባር እንደሚቀይራቸውም ተናግረዋል።
ባለድርሻ አካላቱም የየራሳቸውን ድርሻና ሃላፊነት በመውሰድ ከመናገር ባለፈ የተነሱትን ሀሳቦች ወደ ተግባር ለመቀየር በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
አካዳሚው ከተሰጡት ሶስት ተልዕኮዎች መካከል ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ አመርቂ ውጤት ቢያስመዘግብም የስፖርት ሙያተኞችን አቅም ማጎልበትና ችግር ፈች ጥናት እና ምርምር ስራዎች ላይ የሚጠበቅበትን ያህል አልሰራም ብለዋል።
በሚፈለገው መጠን ያልተሰሩ ስራዎች ላይ የበለጠ ትኩረት በማድረግና ውጤታማ ስራ ለመስራት አካዳሚው አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
ለስፖርቱ ልማት እና እድገት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ እና ዘላቂነት ባለው መልኩ መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ብሔራዊ የስፖርት ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦች፣ አሰልጣኞች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተመርቆ ስራ ከጀመረበት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ቮሊቦል፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋና፣ ቦክስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቅርጫት ኳስ እና ፓራ ሊምፒክ ስፖርቶች ሰልጣኞችን በመመልመል እና በማወዳደር ላይ ይገኛል።
በጥናትና ምርምሩ ረገድም በአካዳሚው አሰልጣኞች እና ሙያተኞች 32፣ በተጋባዥ ሙያተኞች 96፣ በድምሩ 128 ጥናቶችና ምርምሮች ተሰርተዋል።