ባለሥልጣኑ መገናኛ ብዙኃን በሰላም ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ባለሥልጣኑ መገናኛ ብዙኃን በሰላም ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡ አሳሰበ
አዳማ ሚያዝያ 29/ 2011 የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በሰላም ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስለጣን አስገነዘበ።
ከመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሀን ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች በግጭት አዘጋገብና በሰላም ጋዜጠኝነት ዙሪያ የተዘጋጀ ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።
የባለሥልጣኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ በዚህ ወቅት እንዳሳሰቡት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የኅብረተሰቡን ስሜት ከሚኮረክሩ አፍራሽ ዘገባዎች በመፅዳት ሰላምን ለሚያጠናክሩ ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ።
ተቋማቱ የዘርፉ ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበትና በሙያዊ ስነ ምግባር በማነፅ እንዲሁም የተጠያቂነት አሰራርን በማሰፈን የተጀመረውን አገራዊ የመገናኛ ብዙኃን ሪፎርም ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ።
በግጭት አፈታት ዘገባና የሰላም ጋዜጠኝነት ዙሪያ የባለሙያዎችን የመፈጸም አቅም ማሳደግ የሪፎርሙ አንድ አካል መሆኑንም ተናግረዋል።
"መገናኛ ብዙኃን የኅብረተሰቡን ንቃተ ህሊና በማበልጸግ እረገድ የማይተካ ሚና አላቸው" ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ከአገሪቱ ህዝብ ከግማሽ በላይ ቁጥር ያላቸው ሴቶች በግጭት አፈታትና በሰላም እሴት ግንባታ ሚና እንዲኖራቸው ማስቻል የተቋማቱ ቁልፍ ሥራ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል ።
በግጭት ዘገባ ወቅት ተቋማቱና የዘርፉ ሙያተኞች ሊኖራቸው ስለሚገባ ሥነ ምግባር፣ ለዘገባው የሚያስፈልገው ሙያዊ እውቀት እንዲሁም ለሰላም ጋዜጠኝነት ስልጠና መስጠት በሪፎርሙ የተቀመጡ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
"መገናኛ ብዙኃን የግጭት ጉዳዮችን በኃላፊነትና ተጠያቂነት የመዘገብና ፣ለኅብረተሰቡ ስለ ሰላም ግንዛቤ የማስጨበጥ ኃላፊነትና ማስተማር አለባቸው" ያሉት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የአመራርና መልካም አስተዳደር ፕሮግራም ኦፊሰር ወይዘሪት ፀጋ ገብረመስቀል ናቸው።
ተቋማቱ ሴቶች በሰላም ማስፈንና በግጭት አፈታት ያላቸውን ሚና በማጉላት አሳታፊ አሰራር መከተል እንደሚገባውም አመልክተዋል።
"ሰላም የሁሉም ነው" ያሉት ወይዘሪት ፀጋ፣ ለዘላቂ የሰላም እሴት ግንባታ ሴቶችን ከላይ እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን በውሳኔ ሰጪነት ማምጣት ይገባል ብለዋል ።
የመገናኛ ብዙሀንም ግንዛቤ በማስጨበጥ ለተግባራዊነቱ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
"በአገሪቱ የተከናወኑ ሥራዎች ሥርዓተ ጾታን በሚፈለገው መልኩ ያካተቱ አይደሉም" ያሉት ኦፊሰሯ፣ ጋዜጠኞች ስለ ግጭት ሲዘግቡ በዘርፉ እውቀት ያላቸውን ሴቶች ባሳተፈና ኅብረተሰቡን ባማከለ መልኩ መሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።
ለአራት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ከፌዴራልና ከክልል የግልና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች አየተሳተፉ ነው።