ቀጥታ፡

በነቀምቴ ከ205 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መናኽሪያ ሊገነባ ነው

ነቀምቴሚያዝያ 29/2011 በነቀምቴ ከተማ ከ205 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የመናኽሪያ ግንባታ ለማካሄድ ዛሬ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠው በኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሙሌ ደሳለኝና በከተማው ከንቲባ በአቶ ቦጋለ ሹማ ነው።

ወይዘሮ ሙሌ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት በከተማው መናኽሪያው ምዕራብ ኦሮሚያን ጨምሮ ለምዕራቡ የኢትዮጵያ ክፍል ያገለግላል ።

"በሶስት ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባው መናኽሪያ በቀን እሰከ 700 ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል" ብለዋል ።

የመናኸሪያው ግንባታ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል።

መናኽሪያው አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንሰፖርት አገልግሎት ለመስጠት ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ ለዜጎች ሥራ እንደሚፈጥር አስታውቀዋል ።

ከንቲባ አቶ ቦጋለ በበኩላቸው መናኽሪያው ህብረተሰቡን የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል ።

ከተቋራጩ ጋር ስምምነት የፈፀመው የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ግንባታው እስኪጠናቀቅ ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርግ ከንቲባው ጠይቀዋል ።

የነቀምቴ ከተማ ትራንስፖርት ማህበር ሰብሳቢ ሻምበል ዘላለም ብርሃኑ በትራንስፖርት ዘርፍ ያለው ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የባለሃብቶችን ድርሻ ማካተቱን ተናግረዋል ።

"የተሽከርካርዎችን ደህንነት ለመጠበቅና ለመንከባከብ መኽሪያው አስተዋኦው የጎላ በመሆኑ በግንባታው ሂደት ባለንብረቶች የድርሻችን ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል ።

በከተማው የቄሶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ግዛው ሽፈራው ከተማው የንግድ ማዕከል እንደመሆኑ መናኽሪያው ለዘርፉና ለአከባቢው እድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል ።

"መናኽሪያው በሕግና ደንብ የሚመራ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመፍጠር አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል።

ነቀምቴ የምስራቅ ወለጋ ዞን ርዕሰ ከተማ ስትሆን  ከ200ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዳሏት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከኦሮሚያ ክልል ታላላቅ ከተሞች አንዷ የሆነችው ይህቺ ከተማ ምዕራብ ኢትዮጵያም በማገናኘት ቁልፍ ድርሻ እንዳላት ይነገራል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም