የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ሰክሬታሪያት በአዲስ አበባ ሥራውን ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ሰክሬታሪያት በአዲስ አበባ ሥራውን ጀመረ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2011 የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ሴክሬታሪያት በአዲስ አበባ ሥራውን በይፋ ጀመረ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አነሳሽነት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ሴክሬታሪያት በአዲስ አበባ ሥራውን ጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር የዲያስፖራ ትረስት ፈንዱን አማካሪ ምክር ቤት መሰየማቸው ይታወሳል።
በዋና ዳይሬክተር የሚመራው ሰክሬታሪያቱ ደግሞ የፈንዱን ቦርድ ፖሊዎች የመተግበር፣ ፕሮጀክቶችን ለመምረጥ የሚያስችሉ መስፈርቶችን የመቅረፅ ፣ ኃብት ማሰባሰብን ጨምሮ አጠቃላይ የአስተዳደርና ሌሎች የእለት ተእለት ተግባራትን የመከታተልና የመፈፀም ኃላፊነት አለበት።
ሴክሬታሪያቱ በአዲስ አበባ ሥራውን መጀመር ይችል ዘንድ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም እና ከፈንዱ አማካሪ ምክር ቤት ጋር በመተባበር የሰራተኞች ቅጥር መከናወኑን የፈንዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም ገልፀዋል።
የተመድ ልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ሴክሬታሪያትን ለሁለት ዓመት ለመደገፍ ቃል መግባቱንም አመልክተዋል።
በፈንዱ አማካኝነት የሚሰባሰበው ኃብት ሙሉ በሙሉ ለሚቀረፁት የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ እንዲውል የሚደረግ መሆኑንም ፕሮፌሰር አለማየሁ አረጋግጠዋል።
ከዲያስፖራው የሚሰባሰበው ገንዘብ ለሴክሬታሪየቱ የአስተዳደርና ሥራ አመራር ተግባራት ማስፈፀሚያ እንደማይውልም ገልጸዋል።