ቀጥታ፡

በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ለመልሶ ግንባታ ከ306 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

ሚያዝያ 29/2011 በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በተከሰተውን ግጭት የታቀጠሉ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ከ306 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ግብረ ኃይሉ አስታወቀ።

የክልሉ ተፈናቃዮች በዘላቂነት የማቋቋም ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል እንዳሉት ድጋፉ የተሰበሰበው ከአማራ ክልል ነዋሪዎች ፣ ባለሀብቶችና ከክልሉ ውጭ ከሚገኙ የአማራ ክልል ተወላጆች ነው።

የክልል መንግሥትም ተጎጂዎቹን መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።

ተፈናቃዮቹን ለማቋቋም እስካሁን በተደረገው ጥረት በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ 500 ቤቶች መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በተከሰተው ግጭት ከ6 ሺህ 600 በላይ ቤቶች መቃጠላቸውንም ሰብሳቢው አስታውሰዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚደረገው ግንባታ እንዲፋጠን ድጋፉን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

የአማራና የቅማንት ህዝቦች ቀደምት አብሮነታቸውንና ፍቅራቸውን ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ግጭቶችን ያስቆማል የሚል  እምነት እንዳላቸው በአመራር ችግር የተበላሸው ግንኙነት እስኪጠገን ድረስ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ቤታቸው ከተቃጠለባቸው መካከል ወይዘሮ ያጥቢያነሽ መንገሻ በበኩላቸው አካባቢያቸው እየተረጋጋ በመምጣቱ ወደ ቀያቸው ተመልሰው ቤታቸውን ለማስገንባት መወሰናቸውን ተናግረዋል።

''የተቃጠለ ቤቴ በመንግስትና በለጋሽ የኅብረተሰብ ክፍሎች አማካይነት ተገንብቶልኝ እንደ አዲስ ኑሮዬን ጀምሬያለሁ''ያሉት ደግሞ አቶ የሺዋስ ቦጋለ ናቸው።

ከዚህ ቀደም በጉርብትና የነበሩ ሕዝቦች በመካከላቸው የሚገቡ አፍራሽ ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ አብረው ለመኖር መስማማታቸውን ተናግረዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ በበኩላቸው ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው  በሚመለሱበት ወቅት ችግር እንዳይገጥማቸው ሕዝቡና የፀጥታ ዘርፉ  እየሰሩ  መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ከ90ሺህ በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም