ዶክተር አስራት አጸደወይን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆኑ

ጎንደር ሚያዚያ 29/2011 ዶክተር አስራት አጸደወይን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት በመሆን መመረጣቸውን የዩኒቨርሲቲው የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስታወቀ፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ተወካይ አቶ በላይ መስፍን ለኢዜአ እንደተናገሩት ፕሬዘዳንቱ የተመረጡት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአመራራና የአስተዳደር ሃላፊዎችን ለመመደብ ባወጣው መመሪያ መሰረት ነው፡፡

ዶክተር አስራት በፕሬዝደንትነት የተመረጡት ዩኒቨርሲቲው መጋቢት 28 ቀን 2011ዓ.ም መስፈርቱን አሟልተው ለውድድር ከቀረቡ 9 ተወዳዳሪዎች መካከል ባገኙት ከፍተኛ ነጥብ ነው።

ምርጫውን እንዲያስፈፅም ለተሰየመው የዩኒቨርሲቲው ቦርድ አባላትና የውድድር ኮሚቴ ተወዳዳሪዎቹ ባቀረቡት ስትራቴጂያዊ እቅድና ትንተና ዶክተር አስራት በአብላጫ ነጥብ ማለፋቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ዶክተር አስራት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከመምህርነት ጀምሮ በምርምርና ህትመት ዳይሬክተርነት፤ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ፋከልቲ ዲን በመሆን እንዲሁም በአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘደንትነት አገልግለዋል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሂሳብ ትምህርት ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በባዮ ስታስቲክስ የትምህርት ዘርፍ የተከታተሉት ዶክተር አስራት በባዮ ስታስቲክስ የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማእረግም አግኝተዋል፡፡ 

ዶክተር አስራት አጸደወይን በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሚያዚያ 28 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዘደንትነት መሾማቸው ታውቋል፡፡

አዲሱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ለአንጋፋው የጎንደር ዩንቨርሲቲ 5ኛው ፕሬዘዳንት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም