አብሮ የመኖር እሴቶችን በማዳበር ሰላማችንን እንጠብቃለን-- የመቱና ጅማ ከተማ ነዋሪዎች

መቱ/ጅማ ሚያዝያ 28/2011 አብሮ የመኖር መልካም እሴቶችን በማዳበር ሰላማቸውን በአድነት ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ለዘመናት የቆየውን የአንድነትና አብሮነት እሴቶቻቸውን ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን ሴራ በማክሸፍ አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንደሚረባረቡ በኢሉአባቦርና ዞንና በጅማ ከተማ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የብሄር/ብሄረሰብ ተወላጆች ገለጹ።

የዞኑ 13 ወረዳዎችና የጅማ  ከተማ ነዋሪዎች ተወካዮች በአብሮ መኖር እሴቶችና በጋራ አገር ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ ጀምረዋል።

በመቱ ከተማ በተጀመረው ዞናዊ ውይይት ተሳታፊዎች እንደተናገሩት ከለውጡ ወዲህ እንደ ግልና እንደ ቡድን ጥቅሞቻቸው የተነካባቸው አካላት በመካከላቸው ቅራኔና ግጭት በመፍጠር አገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚያደርጉትን ጥረት በጋራ ለመከላከል ዝግጁ ናቸው።

ከጎሬ ከተማ በመድረኩ የተገኙት አቶ ተሰማ አይናለም እንዳሉት ትውልዳቸው አማራ ክልል ቢሆንም ላለፉት 41 አመታት ሀብትና ቤተሰብ በማፍራት  ከአሮሞ ህዝብ ጋር በፍቅር እንደቤተስብ ሆነው እየኖሩ ነው፡

በመሀከላችን ያለውን ስር የሰደደ አንድነትና ፍቅር እኛ ስለምናውቅ ለሴረኞች ቦታ አንሰጥም ያሉት አቶ ተሰማ የአካባቢያቸውን ሰላም በጋራ በመጠበቅ ለአገሪቱ ዕድገት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ከአገራዊው ለውጥ በኋላ ባገኙት ነጻነት እንደ አዲስ የተደራጁ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በሰላምና በፍቅር የሚኖረው ህዝብ መሃል ግጭት ለመፍጠር እያደረጉ ያለው ጥረት እንደሚወገዝ የተናገሩት ደግሞ ከሁሩሙ ወረዳ የመጡት አቶ ጥላሁን ታዬ ናቸው።

''አብሮነታችንና በጋራ የመኖር ባህላችን ስር የሰደደ በመሆኑ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት ውዥንብር በሚፈጥሩ ግለሰቦችና ቡድኖች አይደናቀም'' በማለት ለሰላም  መረጋገጥ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የመቱ ከተማ ነዋሪ አቶ ጫንያለው ሌሊሶ በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ጥርጣሬና መራራቅን በመፍጠር ለውጡን ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን ጥረት ከሁሉም ለማክሸፍ የጋራ ጥረት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

"ከለውጡ ወዲህ በመካከላችን ይበልጥ መቀራረብና አንድነት እየጎለበተ ነው'' ያሉት አቶ ጫንያለው፣ የጥፋት ለልማትና ለሰላም የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።

በሰግለን ኢሉ የመቱ አባገዳ ተሰማ ሙሉነህ እንዳሉት በሀገሪቱ በሁሉም መስኮች የመጣውን ለውጥ ወደ ኋላ ለመመለስ የሚጥሩ ኃይሎች በብሄር ብሄረሰቦችና በእምነት ተቋማት መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ ሴራቸውን ማክሸፍ አለበት ብለዋል።

የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ቡሊ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች የአብሮነትና የአንድነት እሴቶቻቸውን በማጠናከር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በንቃት በመሳተፍ ለእድገት እንዲረባረቡ አሳስበዋል።

በተመሳሳይ በጅማ ከተማ በተጀመረው ተመሳሳይ መድረክ ላይ አብሮ የመኖር መልካም እሴቶችን በማዳበር ሰላማቸውን በአንድነት ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ  ነዋሪዎች አስታውቀዋል፡፡

በከተማው ብሄርብሄረሰቦች የወንድማማችነትና የሰላማዊ ግንኙነት ውይይት መድረክ ''አንድ ነን!' 'በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ከተሳተፉት መካከል ሼክ ጧሊብ ረሸድ ፈጣሪ ለያይቶ የፈጠረን እንድንለያይ ሲሆን እንድንተዋወቅ መሆኑን ቅዱስ ቁርዓን እንደሚያስተምር አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ እየታዩ የሚገኙት ችግሮች ስር ሳይሰዱ መፍትሄ ለመስጠት ሁሉም በከተማው የሚገኙ ብሄር/ብሄረሰቦች በአንድነት መስራት ይገባናል ብለዋል፡፡

መምሬ ሽፈራው በቀለ በበኩላቸው ሰው ለሰው ቀርቶ ለእንስሳት የማዘን ባህልና ኃይማኖት ያለን ህዝቦች በመሆናቸን ጋራ ሰላማችንና አብሮነታችን ማስጠበቅ ይገባናል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ እየተዳከመ የሚገኘውን አብሮ የመኖር እሴቶቻችን እንዲጠናከር መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐመድ በከተማዋ በርካታ  አብረው የሚኖሩ በዋነኝነት ተፈጥራዊ በሆነ የሰው ልጅ እንቅስቃሴ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በአንዱ ቤት የእሳት አደጋ፣ የጎርፍ አደጋ፣ ኃዘን፣ህመም ሲያጋጥም ሰው የሚረዳዳውና አብሮ የሚያዘነው ብሄር ወይም ኃይማኖት እየተጠየቀ አለመሆኑንም አመልከተዋል፡፡

በደስታውም ጊዜ አብሮ የሚደሰተው እንደ እቁብ፣ እድር የመሳሰሉትም ማህበራዊ ተቋማትን እየመሰረተ የሚኖረው ያለምንም ልዩነት እንደሆነም ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎች የሕግ የበላይነት እንዲሰፍንና ሰላምን ለማስፈን እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡

በከተማ አስተዳደር ደረጃ የተጀመረው ወይይት በቀጣይ በሁሉም ቀበሌዎች ይካሄዳል፡፡

በውይይቱ ላይ አባገዳዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣የአገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶችና በጅማ ከተማ የሚኖሩ ብሄር/ ብሄረሰቦች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም