ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአቪየሽን ዘርፍ የካበተ ልምዷን ለሌሎች አገሮችም ማጋራቷን ቀጥላለች

ሚያዝያ 28/2011 ኢትዮጵያ በሲቪል አቪየሽን ዘርፍ ያካበተችውን ልምድ ለሌሎች አገሮችም ማጋራቷን መቀጠሏ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ሲሺል አቪየሽን ባለስልጣን ሰባት የሶማሊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎችን ተቀብሎ ስልጠናውን በዛሬው እለት መስጠት ጀምሯል።

የኢፌዲሪ ትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂወት ሞሲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በሲቪል አቪየሽን መስክ ያላትን ልምድና ተሞክሮ ተጠቅማ ብቃት ያለው የሰው ኃይል በመፍጠት ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በአቪየሽን ዘርፍ ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደረጋት ሲሆን ይህን ልምድና ተሞክሮ ለማጋራት ለጎረቤት አገሮች ስልጠናዎችን መስጠቷን ቀጥላለች።

በሲቪል አቪየሽን መስክ የሰለጡኑና ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ማፍራት ለቀጠናው ውህደትም ጠቃሚ መሆኑንም ወይዘሮ ሂወት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሶማሊያ ምክትል አምባሳደር ሚስተር ፋራ አሊ መሃመድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ሶማሊያን ለመደገፍና እርዳታ ለማድረግ እያደረገ ላለው ጥረት ምስጋና አቅርበው ስልጠናው ሁሉን አቀፍ ውህደት ለመፍጠር ወሳኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኩል በቀጠናው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትብብር ለመፍጠር እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኝነትን ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት ያግዛል ብለዋል።

ስልጠናው ክህሎትን፣ እውቀትን፣ሞራልንና በራስ መተማመንን ለመጨመር ወሰኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረው በቀጣይም መሰል ትብብሮች ተጠናቅረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት አክለዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ በምታሳየው ውጤት አለም አቀፉ የአቪየሽን ባለስልጣን ጭምር ለስልጠና እየመረጣት ይገኛል።

አቪየሽኑ እስካሁን ለሶማሌላንድና ለጅቢቲ ሲቪል አቪየሽን ባለሙያዎች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ለሶማሊያ አቪየሽን ባለሙያዎችን ደግሞ ለስምት ሳምንታት የሚሰጠውን ስልጠና ዛሬ ጀምሯል።

በስልጠናው ቀጣይ ሌሎች ጎረቤት አገሮችንም በማዳረስና ቀጠናዊ ውህደትን ለማጠናከር የስልጠና ማዕከሉን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም