ቀጥታ፡

የደሴ ከተማና ወሎ ኮምቦልቻ ጨዋታ በጸጥታ ችግር ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተራዘመ

ሚያዝያ 28/2011 በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሚጫወቱት የደሴ ከተማና የወሎ ኮምቦልቻ የእግር ኳስ ክለብ ጨዋታ በጸጥታ ችግር ምክንያት ለሌላ ጊዜ መራዘሙን የኮምቦልቻ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በሁለቱ ክለቦች መካከል ትናንት በኮምቦልቻ ስታዲየም የተጀመረው ጨዋታ በደጋፊዎች አለመግባባት በተፈጠረ የጸጥታ ችግር 35ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጧል፡፡

የኮምቦልቻ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ያለለት ዘገዬ እንደገለጹት ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ዉይይት ዛሬ አራት ሰዓት ላይ በኮምቦልቻ ስታዲየም በዝግ ጨዋታዉ እንዲካሄድ ተወስኖ ነበር።

ነገር ግን ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ በከተማው ባለዉ የጸጥታ ስጋት ምክንያት ጨዋታው እንዳይካሄድ ዉሳኔ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

ወጣቱ በጉልበት "ወደ ስታዲየሙ እንገባለን፣ በሜዳችን ላይ በዝግ መካሄድ የለበትም" በሚል በዋና ዋና መንገዶች ላይ በመፈጠሩት ግርግር ምክንያት ለከተማዉ ሰላም ሲባል ጨዋታው ለሌላ ጊዜ ተራዝሟል" ብለዋል።

በሁለቱ ወንድማማቾች መካከል እንዲህ አይነት አስነዋሪ ተግባር መፈጸሙ አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በትናንትናው ለዕለት በተፈጠረ የደጋፊዎች ብጥብጥም በተለያየ አቅጣጫ በተወረወረ ድንጋይ በተመልካቾች ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ችግሩን በመከላከያ ሠራዊትና በልዩ ኃይል አባላት በፍጥነት መቆጣጠር እንደተቻለም አስታውቀዋል፡፡

ጨዋታዉ መቼና እንዴት መካሄድ እንዳለበት አግባብ ባላቸው አካላት እንደሚገለጽም ኮማንደር ያለለት አስታውቀዋል፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም