ቀጥታ፡

ድሬዳዋ ከነማ ወላይታ ዲቻን 2 ለ 1 አሸነፈ


ድሬዳዋ ሚያዝያ 27/2011 ድሬዳዋ ከነማ በሜዳው ወላይታ ዲቻን አስተናግዶ ሁለት ለአንድ አሸነፈ።

ደረጃውን ወደ ዘጠነኛ ከፍ ያደረገው የድሬ ከነማ ዋና አሰልጣኝ "ጠንክረን በመስራት የተሻለ ደረጃ ይዘን ለማጠናቀቅ እንተጋለን" ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዛሬ የተገናኙት ክለቦች በመጀመሪያ ግማሽ ያደረጉት ጨዋታ የተመልካቹ ስሜት መግዛት ባይችልም፤ ሦስት ግቦች የተቆጠሩበት ነበር፡፡

 ወላይታ ዲቻ በስድሰተኛው ደቂቃ ላይ ከማዕአዘን የተሻገረችን ኳስ በተስፋዬ አለባቸውአማካይነት  አስቆጥሮ መምራት ቢችልም፣ የከነማው ረመዳን ናስር በ15ኛው ደቂቃ አካባቢ ከ40 ሜትር ርቀት አክሮ የመታት ድንቅ ኳስ አጨቃጫቂ ግብ  ሆናለች፡፡

ኳሷ‹‹ ጎል አልገባችም››በሚል የዲቻ ተጫዋቾችና አሰልጣኞችከመሐል ዳኛዋ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡

የከነማው ረመዳን ናስር በ36ኛው ደቂቃ  ከማዕዘን የተሻገረችን ኳስ  አስቆጥሮ ድሬ ከነማ ሁለት  ለአንድ መምራት ቻለ፡፡

ወላይታ ዲቻ የተሻለ እንቅስቃሴ ባደረገበት በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም በቡድኖች ግብ ለማግባት ሙከራ ቢያደርጉም፤ሳይሳካለቸው ቀርቷል፡፡

ከጨዋታው በኋላ የድሬ ከነማ ዋና አሰልጣኝ ስምኦን አባይ ለጋዜጠኞች ''ሁለታችንም በጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘትእንፈልግ ነበር እኛ ግን አሳክተናል'' ብለዋል፡፡

''ከእረፍት በኃላ ተጭነውን ተጫውተው ነበር፤ ተከላካይ ክፍሌ ጠንካራ በመሆኑ ጎል(ግብ) ማስቆጠር አልቻለም››ብለዋል፡፡

በቀሪ ጨዋታዎች ጠንክረው በመስራትና በመጫወት የተሻለ ደረጃ ይዘው እንደሚያጠናቅቁም ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ድሬ ከነማ ዛሬ በማሸነፉ ከነበረበት 11 ደረጃ ወደ ዘጠነኛ ከፍ ብሏል ፡፡

የወላይታ ዲቻ ዋና አስልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጨዋታውን አስመልክተው ምንም መናገር  እንደማይፈልጉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ መቀሌ ሰባ እንደርታ በ48 ነጥብ በመምራት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም