የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላትን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላትን አስመረቀ
ሐዋሳ ሚያዝያ 27/2011 የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ ከአንድ ሺህ በላይ የልዩ ኃይል ፖሊስ ሠልጣኞችን ዛሬ አስመረቀ፡፡
በብላቴ ልዩ ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል የሰለጠኑት አባላት ለስድስት ወራት የንድፈ ሀሳብና የተግባር ሥልጠናዎችን ተከታትለዋል፡፡
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤልያስ ሽኩር የፖሊስ አካላት ተልዕኮ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስከበርና ህዝቡን ከጥቃት መጠበቅ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ከዳር ማድረስ ጠንካራ፣ብቁና ገለልተኛ ፖሊስ እንደሚያስፈልግ አመልክተው፣የክልሉን ፖሊስ አወቃቀር በአሰራርና በአደረጃጀት በማስተካከል ተልዕኮውን እንዲወጣ ሪፎርም እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለምረቃ የበቃው የፖሊስ ኃይልም የሪፎርሙ አንድ አካል መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
ሪፎርሙ በፖሊስ መዋቅር ውስጥ ዕርካታን ያልፈጠሩ ጉዳዮችንና ጥያቄዎችን ለመፍታት እንዳለመም አቶ ኤልያስ አመልክተዋል፡፡
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ቴዎድሮስ ወልደሚካኤል የአገሪቱን ሠላም ብሎም የህዝቡን ሕይወትና ንብረት በዘላቂነት የሚጠበቀው ፖሊስ ከፖለቲካ፣ ብሔርና ሐይማኖት ወገንተኝነት ራሳቸውን እንዲያርቁ አሳስበዋል፡፡
ተመራቂዎች ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ኅብረ ብሔራዊነትን በጠበቀ መልኩ መመልመላቸውን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ፖሊስ ኮሌጅ ዘርፍ ኃላፊ ኮማንደር ጁሃር ሙሳ ኮሌጁ ከ2008 ጀምሮ በፖሊስ ሳይንስ ዲፕሎማ መርሀ ግብር አጩ መኮንኖችን ተቀብሎ እያሰለጠነ መሆኑን ገልጸው፣ የዲግሪ መርሐ ግብርም በቅርቡ ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ ከመስጠት ባሻገርም ተቋሙን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ለውጡን ለማስቀጠል መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
ከተመራቂ ሠልጣኞች መካከል ኮንስታብል መቅደስ ሚልኪያስ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የሚያስችላት ሥነ-ልቡናዊና አካላዊ ሥልጠና መከታተሏን ተናግራለች፡፡
ከአድሏዊና ብሔርተኝነት በፀዳ መልኩ ሙያዊ ግዴታዋን ሕገ መንግሥቱን ለማስከበር ዝግጁ መሆኗንም ገልጻለች፡፡
ሌላው ተመራቂ ኮንስታብል መለሰ መጃ በበኩሉ ሙያዊ ግዳጁን ዜጎች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በማገልገል ለመወጣትመጋጀቱን አስታውቋል፡፡
ለምረቃ ከበቁት 1 ሺህ 467 ሠልጣኞች መካከል 233 ሴቶች ናቸው፡፡
በመርሐ-ግብሩ ላይ የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ተገኝተዋል።