ጃፓንና ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ጃፓንና ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክረው ይቀጥላሉ
ሚያዝያ 27/2011 ጃፓንና ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክረው ለመቀጠል ተስማሙ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌና የጃፓኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታሮ ካኖ ዛሬ በሁለትዮሸ ግንኙነት ላይ መክረዋል።
ሚኒስትሮቹ በሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነትና በአህጉር አቀፍና አለም ዓቀፍ ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ማርቆስ በዚሁ ጊዜ በሁለቱ አገሮች መካከል ረጅም ዘመን ያስቆጠረውን ግንኙነት በማድነቅ ጃፓን የኢትዮጵያ የልማት አጋር ከሆኑ ቀዳሚ አገሮች አንዷ መሆኗንም ጠቅሰዋል።
የጃፓን መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የልማት ድጋፍም አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አመራር ያስመዘገበችውን ተጨባጭ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ለውጥን በተመለከተም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አብራርተውላቸዋል።
ከነዚህ መካካል የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣የሚዲያ ነፃነትን በማረጋገጥ እና የተቋማትን አቅም በመገንባት በኩል የተከናወኑ ተግባራትን ጠቅሰዋል።
የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታሮ ካኖ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አድንቀው በዚህ በኩል ኢትዮጵያ የያዘችውን ግብ እንድታሳካ ጃፓን ሙሉ ድጋፏን ትቀጥላለች ብለዋል።
ኢትዮጵያና ጃፓን ያላቸውን የንግድ ፣ የኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም ግንኙነት በስፋት አጠናክረው መቀጠል አለባቸውም ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጨምረው እንደገለጹት የሁለቱን አገሮች ህዝቦች በጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ በአገራቱ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ማሳደግ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን የምታከናውነውን ገንቢ ሚናንም በእጅጉ አድንቀዋል።
ጃፓን በአህጉሪቱ ሰላምና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ከኢትዮጵያና ከሌሎች ባለድርሻ አገራት ጋር ተቀራርባ ትሰራለችም ብለዋል።