ቀጥታ፡

በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሽኝት የተለያዩ ሰዎች መልዕክት አስተላልፈዋል

አዲስ አበባ ሚያዚያ 27/2011 የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አስክሬን ሽኝት በሚሊኒየም አደራሽ ተካሄዷል።

የኢፌዲሪ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህይወት ቢያልም የታገሉለት ዓላማ ፍሬው ህያው ሆኖ ይቀራል ሲሉ የቅርብ ወዳጆቻቸው ተናገሩ።

አቶ አስራት ጣሴ፣ አቶ ሌንጮ ለታና ሌሎች የቅርብ ወዳጆቻቸው ስለ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሰብዕናና ፍትህን ለማስፈን የሰሯቸውን ተግባራት አውስተዋል።

አቶ ሌንጮ ለታ ዶክተር ነጋሶ ለዓላማቸው ጽኑና ለስኬቱም መስዋዕት የሚከፍሉ እንደነበሩ በንግግራቸው አንሰተዋል።

አቶ አስራት በበኩላቸው ዶክተር ነጋሶ ህይወታችው ቢያልፍም በህይወት ዘመናቸው ያከናወኗቸው ስራቸው ህያው ሆኖ እንደሚቀር ነው ያወሱት።

አሁን በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ ለውጦች ዶክተር ነጋሶ ከታገሉላቸው ዓላማዎች ውጤት መሆናቸውን በማንሳት የሰሩት በጎ ተግባር ህያው ሆኖ ይቀራልም ብለዋል አቶ አስራት።

በሽኝቱ ላይ ሃይማኖታዊ የጾሎት ስነ-ስርዓት የተደረገላቸው ሲሆን የህይወት ታሪካቸውም ተነቧል።

 ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የኤፌዴሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና  ሌሎች የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።

 የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ባለቤታቸውና ልጆቻቸውም ንግግር አድርገዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሃዘን መግለጫ ንግግር በማድረግና ሌሎች መርሃ ግብሮች ተከናውነው አስከሬናቸው የቀብር ስነ ስርዓቱ ወደ ሚፈጸምበት ጴጥሮስ ወጳውሎስ የቀብር ስፍራ ይሸኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም