በኢትዮጵያ የአህዮች እድሜ ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነፃፀር በግማሽ ያነሰ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የአህዮች እድሜ ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነፃፀር በግማሽ ያነሰ ነው
ሚያዝያ 27/2011 የኢትዮጵያን አህዮች በህይወት የመኖር አማካይ ዕድሜ ከ9 ወደ 15 ዓመት ማሳደግ ቢቻልም ከሌሎች ሀገራት አህዮች ጋር ሲነፃፀር በግማሽ ያነሰ መሆኑን የጋማ ከብቶች ደህንነትና እንክብካቤ ፕሮጀክት ገለፀ።
በአዲስ አበባ መርካቶ ብቻ በቀን በአማካይ 3 ሺህ አህዮች ገብተው ይወጣሉ ተብሏል ።
የጋማ ከብቶች ደህንነትና እንክብካቤ ፕሮጀክት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ፈንታ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት ኢትዮጵያ በአህያ ሀብቶቿ ቁጥር ከዓለም የአንደኝነቱን ደረጃን ተረክባለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ የአህዮች ቁጥር ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወደ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን በማደጉ ከዓለም የአንደኛነቱን ደረጃ 6 ሚሊዮን አህዮች ካሏት ቻይና ተረክባለች ።
ኢትዮጵያ አምስት ዓይነት የአህያ ዝርያዎች ሀብት የያዘች አገር ስትሆን በመካከለኛውና በሰሜን የሃገራችን ክፍል በብዛት የሚገኘው የአህያ ዝርያ አቢሲኒያ ዶንኪ በመባል እንደሚታወቅ ሃላፊው ተናግረዋል ።
ሌሎቹ የአህያ ዝርያዎች ጅማ ፣ ሲርና ፣ ኦጋዴንና ሲናር ዶንኪዎች በመባል ይታወቃሉ ።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አህዮች በህይወት የመኖር አማካይ ዕድሜ ባለፉት 20 ዓመታት ከ9 ዓመት ወደ 15 ዓመት ከፍ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም ከሌሎች አገራት አህዮች ጋር ሲነፃፀር አሁንም ከግማሽ ያነሰ መሆኑን አቶ አለማየሁ ይናገራሉ ።
በአደጉ አገራት የአህያ አማካይ ዕድሜ 37 ዓመት ፣ መካከለኛ ገቢ ባለቸው አገራት ደግሞ 25 ዓመት መሆኑን ከሃላፊው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።
የአገራችን አህዮች አመጋገብ አያያዝና የአጠቃቀም ጉድለት ቀጫጫና እድሜያቸውንም አጭር እንዳደረገው የገለጹት አቶ አለማየሁ ፕሮጀክቱ በ1986 ዓ.ም ከተቋቋመ ወዲህ ለአህዮች የተሻለ ህክምናና ክብካቤ መደረጉ አንጻራዊ መሻሻል መታየቱን ተናግረዋል።
“በውስጥና በውጭ ተህዋሲያን በቀላሉ የሚጠቁ በመሆናቸውም በላቦራቶሪ የታገዘ በዓመት ለሁለት ጊዜ በአማካይ ለ170 አህዮች ህክምና ይሰጣል” ብለዋል ።
ቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የፕሮጀክቱ ዋና መስሪያ ቤት ከወሊድ ጋር የተያያዘም በዓመት በአማካይ 8 አህዮች በወፍራም ፍራሽ ተኝተው የቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎት እንደሚያገኙ ተናግረዋል ።
ለችግር የተጋለጡ አህዮች በፍጥነት ደርሶ ወደ ማእከሉ በማምጣት የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ የሚያግዝ የአህዮች ማመላለሽ አምቡላስ አለው ተብሏል ።
በአዲስ አበባ መርካቶ ብቻ በቀን በአማካይ 3 ሺህ አህዮች ገብተው ስለሚወጡና በስራ ጫና ፣ በአጠቃቀም ጉድለትና በእንክብካቤ ማነስ በተለያዩ በሽታዎች በተለይ ደግሞ ለመቁሰል አዳጋ የተጋለጡ በመሆናቸው በአካባቢው የአህዮች ህክምና ማእከል መቋቋሙን ሃላፊው አስረድተዋል ።
በአገራችን በተለይ ደግሞ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ አህዮችን ከክብደታቸው በላይ እንዲሸከሙ ማድረግ እድሜያቸው ለማጠር ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡
የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖለስ መምሪያ የትራፊክ ደህንነት ዲቪዥን ሃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር እስማኤል አባድር እንደገለፁት በዞኑ ስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች በአህያ ጋሪ ላይ ዕቃና ከ11 ሰዎች በላይ በመጫን በእንሰሳት ሃብቱ ላይ ያልተገባ ጉዳት የሚደርስበት አጋጣሚ አለ።
አልፎ አልፎም ጋሪ ከጋሪና ጋሪ ከተሽከርካሪ ጋር እየተጋጨ በሰውና በአንሰሳት ህይወት ላይ የሞት አደጋ እንደሚያጋጥም የገለፁት ምክትል ኢንስፔክተሩ እንስሳቱን በአግባቡ በመጠቀም እየደረሰ ያለውን ጉዳት መቀነስ አንደሚቻል ምክር ለግሰዋል ።